የምክክር ጉባኤው ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ መፍትሔ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ መፍትሔ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ ትልቅ መፍትሔ እንደሚያመጣ ተስፋ አለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
በሀገራዊ ምክክሩ ለምክክር የተመረጡት አጀንዳዎች ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ መልኩ በመገንባት ልማትን ከማረጋገጥ አንጻር አሉታዊ ተጽእኖ ሲፈጥሩ የቆዩ መሆናቸው ይታወቃል።
እነዚህን ችግሮች አካታች እና አሳታፊ በሆነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመምከር ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።
ኢዜአ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ለሀገር ልማትና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ተዘዋውሮ አነጋግሯል።
ኢትዮጵያ የአኩሪ ታሪኮች ባለቤት መሆኗን ጠቁመው በዛው ልክ ደግሞ ልዩነት በሚስተዋልባቸው አጀንዳዎች ላይ ከመመካከር ይልቅ የኃይል አማራጭን እንደመፍትሄ የመውሰድ አካሄድ ኢትዮጵያን ዋጋ ሲያስከፍላት ቆይቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እያካሄደች መሆኑ የሃሳብ ልዩነት ሲታይባቸው ለቆዩ ችግሮች የጋራ መፍትሔ በማስቀመጥ ለሀገራዊ ልማትና ዘላቂ ሰላም መጎልበት አይነተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪው ቀናው አይቸው እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር የልዩነት ምንጭ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በሰለጠነ መንገድ በመመካከር የጋራ የመግባባት ላይ ለመድረስ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በየጊዜው ከሚያጋጥሟት ፈተናዎች ተላቃ የጀመረችውን የልማት እና የብልጽግና ጉዞ አጠናክራ እንድትቀጥል ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑንም አክለዋል።
እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ አቅም መፍታት የምትችልበትን ልምድ እንደሚያጎለብትም ገልጸዋል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በቀረቡት ስምንት አጀንዳዎች ላይ በመምከር የጋራ መግባባት ላይ እየደረሱ መሆኑንም አክለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን ሁላችን ከምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦች ለሀገር የሚኖራቸው ፋይዳ እውን እንዲሆን ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የቆዩ ችግሮች ላይ ምክክር ሳታደርግ ያሳለፈቻቸው ጊዜያት ቢኖሩም ዛሬ ላይ ምክክር እየተካሄደ መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪው ከፍያለው በላይ ናቸው።
ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገር እድገት እንቅፋት ሆነው የቆዩ ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ ሚናው የጎላ እንደሆነም አንስተዋል።
ምክክሩ ለሀገር በሚጠቅም መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ከመገናኛ ብዙሃን መገንዘባቸውን ጠቁመው በቀጣይም ለችግሮች መፍትሄ የሚሰጥ ውጤት እንደሚመጣ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑት መኮንን መገርሳ በበኩላቸው ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከርና ምጣኔ ሃብታዊ እድገትን ለማፋጠን ምክክርን መነሻ ያደረገ አካሄድ መከተል ጠቃሚ ነው ብለዋል።
ምክክሩ ልዩነት በሚፈጥሩ ጉዳዮቻችን ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበን በመምከር ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል ትምህርት የቀሰምንበት እና ምክክር ባህል እንዲሆን ያስቻለ ነው ሲሉም አክለዋል።
በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ምክክሩ አይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ በቀጣይም በሀገራዊ አጀንዳዎቻችን ዙሪያ አሳታፊና አካታች ምክክር በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ የመድረስ ባህልን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አዲሱ ከተማ ሀገራዊ አንድነታችንን ያጠናከሩና በህብረት ያሳካናቸው አኩሪ ተሪኮች ባለቤት ነን ያሉ ሲሆን በማያግባቡ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የምክክርን ባህል ባለማድረጋችን ሀገሪቱን ለችግር ስናጋልጥ ቆይተናል ብለዋል።
አሁን እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ ምክክር የልዩነት ምንጭ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ በሰለጠነ መንገድ በመመካከር ዘላቂ የመፍትሄ ሀሳቦች መለየታቸው ሀገር ወደ ተሻለ እድገት ጎዳና እንድትጓዝ ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ በአጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባትንና አንድነትን የሚያጠናክር ውጤት እንደሚገኝበት ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።