ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት በመሸጥ የሻዕቢያና የግብፅ ታማኝ ቅጥረኛ መሆኑን በተግባርእያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት በመሸጥ የሻዕቢያና የግብፅ ታማኝ ቅጥረኛ መሆኑን በተግባርእያሳየ ነው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ) ፦ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት በመሸጥ የሻዕቢያና የግብፅ ታማኝ ቅጥረኛ መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት የቀድሞ አባል ኮሎኔል ገብረዋህድ ኃይሉ ገለጹ ።
የ’’ፅምዶ” መሪዎችና ባለቤቶችም ግብፅና ሻዕቢያ ሲሆኑ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ኋላቀር ቡድን ደግሞ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪና ዓላማ አስፈጻሚ መሆኑንም አጋልጠዋል።
ኮሎኔል ገብረዋህድ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይን ሕዝብ እንደ ግል ንብረቱ በመቁጠር ለከፋ ጉስቁልና እየዳረገው ይገኛል።
ሕገ-ወጥ ቡድኑ’’ፅምዶ” በሚል ስያሜ ከሀገር ውስጥ ፅንፈኛ ኃይሎችና ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚያደርገው የክህደት እንቅስቃሴም ሀገርን ለማጎሳቆል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያን መዳከም የሰርክ ሥራቸው ያደረጉትን የሻዕቢያና የግብፅን የጥፋት ዓላማ በማንገብ የትግራይ ክልል ወጣቶችን ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የትግራይ ክልልን ሕዝብ የሰላምና የልማት ፍላጎት ምላሽ የሰጠ ታሪካዊ የሰላም ውልና ፀጋ መሆኑን አስታውሰዋል።
ሕገ-ወጥ ቡድኑም አሁን ላይ የክልሉን ህዝብ ሰላምና እፎይታን ያጎናፀፈውን ስምምነት በማደናቀፍ የራሱን ሥርዓት አልበኛና አምባገነናዊ አስተዳደር መፍጠሩን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ህዝብ በሕገ-ወጡ ቡድኑ የጥፋት እንቅስቃሴ የከፋ ስቃይና እንግልት እያስተናገደ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተለይም በሥርዓት አልበኛ እንቅስቃሴው ወጣቶችን በአስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የትግራይ ክልል እናቶችን ለከፍተኛ ስቃይ እየዳረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የትግራይ ክልል እናቶች በሕገ-ወጥ ቡድኑ ላይ የሚያደርጉት ተቃውሞም በእስርና አፈና በማዋረድ ጭምር በማፈን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እየፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሕገ-ወጥ ቡድኑ እንቅስቃሴ ሕገ-መንግሥቱን፣ የሕዝብን ፍላጎትና የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት በመቃረን ለውጭ ታሪካዊ ጠላቶችና ኃይሎች በጥፋት መሳሪያነት ለማገልገል እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የ’’ፅምዶ” መሪዎችና ባለቤቶች ግብፅና ሻዕቢያ ናቸው ያሉት ኮሎኔል ገብረዋህድ፤ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ኋላቀር ቡድን ደግሞ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪና ዓላማ አስፈጻሚ ነው ብለዋል።
በሌላ መልኩም ሕገ-ወጡ ቡድን በትግራይ ክልል ወጣቶች ላይ የሚፈፅመው አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳም ሻዕቢያ የሚጠቀምበትን ኢ-ሰብዓዊ አስተሳሰብ እየተከተለ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የሕገ-ወጡ ሕወሓት ቡድን ጋላቢ የሆነው ሻዕቢያም በዋናነት የትግራይ ክልል ህዝብን እንዲሁም የኤርትራን ህዝብ ለከፋ ስደትና ስቃይ የሚዳርግ ጨካኝና ፀረ-ዴሞክራሲ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሕገ-ወጡ ሕወሓት በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ኢ-ሰብዓዊ በደል ከፈፀመው ሻዕቢያ ጋር ’’ፅምዶ’’ በሚል ስያሜ የፈጠረው ያልተቀደሰ ጋብቻም በህዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥፋት እንቅስቃሴ መሆኑን አንስተዋል።
የትግራይ ክልልን ሕዝብ እንደ ግል ንብረቱ በመቁጠር ጭምር የሕፃናትና ወጣቶችን ነፍስም እንደተራ ሸቀጥ ከራሱ የጥፋት ዓላማ ባሻገር ለውጭ ገበያ በማቅረብ የጦርነት ሰለባ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሕገ-ወጥ ቡድኑ ጥቂት ስብስቦችም በውጭ ጠላቶች እየታዘዙ የሕዝብ ጉስቁልናን ከቁብ የማይቆጥሩ የለውጥ አስተሳሰብ የተነፈጋቸው አካላት መሆናቸውን አብራርተዋል።
ቡድኑ የትግራይ ክልል ሕፃናትና ወጣቶችን ከእናትና ቤተሰቦቻቸው ጉያ በመንጠቅ በሚፈፅመው አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳም ለሕዝብ ደንታ እንደሌለው በተግባር እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
የትግራይ ክልል ሕዝብም የሕገ-ወጡን የሕወሓት ቡድን የጥፋት እንቅስቃሴ በመፀየፍ በግልፅ እየተጋፈጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የክልሉን ሕዝብ የጥፋት መንገድን አማራጭ ካደረገው የሕገ-ወጥ ቡድን የግፍና የመከራ ቀንበር ለማላቀቅም ቀጣይነት ያለው ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።