ቀጥታ፡

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትብብርና ተሳትፏችን ተጠናክሮ ይቀጥላል- ወጣቶች

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፡- በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

በባህር ዳር ከተማ በርካታ ወጣቶች ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመሆን የአረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩ ሲሆን ከበጎ ፈቃድና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር ከተሳተፉት ወጣቶች መካከል ወጣት ዘላለም ታከለ፤ በበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበረሰብን በነፃ የማገልገል እድል በማግኘቱ መደሰቱን ገልጿል።

የመተባበር፣ የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህሎችን በማስፋት በተለይም አቅመ ደካሞችን ማገዝ መቀጠል ያለበት መልካም እሴት መሆኑን አንስቶ በአረንጓዴ ልማትና ሌሎችም መርሃ ግብሮች በሀገር ልማት ላይ መሳተፍ መቻል አስደሳች መሆኑን አንስቷል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግሯል።

በቀጣይም በከተማዋ ለሚከናወኑ በጎ ተግባራት ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ሌላው ወጣት በላይነህ ደጉ፤ ከኢዜአ ጋር በመሆን በችግኝ ተከላ አሻራውን ማኖሩን ገልጾ በክረምቱ በተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግሯል።

በቀጣይም በክረምትም ይሁን በበጋ ማህበረሰብን በነፃ ለማገልገል በሚደረገው ጥረትና በሀገር ልማት ላይ ተሳትፎውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከቀናት በፊት በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በባህር ዳር ከተማ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ማስጀመሩ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም