መንግስት ለኪነ-ጥበብ ዘርፍ ዕድገት የሰጠው ትኩረት ተተኪ ባለሙያዎችን በስፋት ለማፍራት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለኪነ-ጥበብ ዘርፍ ዕድገት የሰጠው ትኩረት ተተኪ ባለሙያዎችን በስፋት ለማፍራት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦መንግስት ለኪነ-ጥበብ ዘርፍ ዕድገት የሰጠው ትኩረት ተተኪ ባለሙያዎችን በስፋት ለማፍራት ትልቅ ዕድል መፍጠሩን አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ገለጹ።
የኪነ-ጥበብ ዘርፉ ከሀገር ጋር ተመጣጣኝ ዕድገት እንዲያስመዘግብ በመንግስት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ኪነ-ጥበብ የአንድ ሀገር ማንነት፣ ታሪክና እሴት ማንጸባረቂያ ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ እድገትና ለስራ ዕድል ፈጠራ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ዘርፍ ነው።
መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘርፉን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፣ ይህም ዘርፉ በመንግስት ልዩ ትኩረት እያገኘ መምጣቱን እንደሚያመላክት ኢዜአ ያነጋገራቸው አንጋፋ አርቲስቶች ገልጸዋል፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኪነጥበቡን የሚያሳድጉ የአዳዲስ ቴአትር ቤቶች ግንባታ እና እድሳት ስራዎች እንዲሁም ዘርፉን የሚያነቃቁ ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛሉ።
ይህም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የጥበብ ስራዎቻቸውን ወቅቱ የፈጠራቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በተገነቡ እና በተጠገኑ መሠረተ ልማቶች ታግዘው እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
መንግስት ለዘረፉ ዕድገት የሰጠው ትኩረት ኪነ-ጥበብ ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለቱሪዝም መስፋፋትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ የምታበረክተውን አስተዋጽኦ እንድታሳድግ ያስችላል።
ይህ የመንግስት ትኩረት ለተተኪ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መፍለቅ ተስፋ የሚሰጥና በስራዎቻቸውም መነሳሳት እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አርቲስት ተፈሪ አለሙ መንግስት አዳዲስ ቴአትር ቤቶችን መገንባቱና ነባሮቹንም ለማዘመን እያከናወናቸው የሚገኙት ተግባራት ለኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪው ዕድገት ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው ብሏል፡፡
መንግስት ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት እና እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንደ ትልቅ ዕድል በመጠቀም የዘርፉ ባለሞያዎችም በመንግስት በሚደረገው ድጋፍ ልክ ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል ነው ያለው፡፡
የኪነ-ጥበብ ዘርፉ ከከተማው ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ዕድገት እንዲያስመዘግብ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያለውን እምነት ጠቅሷል፡፡
ሌላኛዋ አንጋፋ አርቲስት አለምፀሃይ ወዳጆ እንደገለጸችው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት የኪነ-ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለሙያው ትኩረት መስጠቱን ያመላክታል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ እየተገነቡ የሚገኙት አምፊ ቴአትሮችና አዳዲስ ቴአትር ቤቶች ግንባታና የነባር ቴአትር ቤቶችን ለማዘመን እየተደረገ ያለው ጥረት እንዳስደሰታትም ተናግራለች፡፡
ይህ የመንግስት ትኩረት በዘርፉ አዳዲስ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጻለች፡፡
መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያው ዘርፉን ለማሳደግ የሚያደርጉት ርብርብ ለዘርፉ ዕድገት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሳለች፡፡