ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማትና የፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ የደብረ ብርሃን ከተማን ለኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተመራጭ እያደረጓት ነው

ደብረ ብርሃን፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፡-የኮሪደር ልማትና የፅዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ የደብረ ብርሃን ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ተመራጭ እያደረጓት መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማ አስተዳደሩ የምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት፣ የአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የጽዳትና ውበት ተጠሪ ጽሕፈት ቤቶች “ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ” በሚል መሪ ሐሳብ የጋራ የንቅናቄ መድረክ አካሂደዋል።

በመድረኩም የከተማዋ ነዋሪዎች፤ የኮሪደር ልማትና የፅዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ የደብረ ብርሃን ከተማን ለኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተመራጭ እያደረጓት ነው ብለዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ደስታ ፀጋ፤ በከተማው የተተገበረው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ አድርጓታል ብለዋል። 

ነዋሪዎችም የአካባቢያቸውን ጽዳትና ንጽህና በመጠበቅ የከተማዋን እድገት ለማፋጠን የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ገነት ሀይለሚካኤል በበኩላቸው፤ አስተዳደሩ የከተማዋን ሰላም ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ዘላቂ እድገትን የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን እየከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። 

በከተማው እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማትና የፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ተግባራት ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የከተማዋን ገጽታ ይበልጥ ለማድመቅም ከራስ ግቢ እስከ ዋናው መንገድ ያለውን በማህበረሰብ ተሳትፎ በማፅዳት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ አማካሪ አቶ ታጠቅ ገድለአማኑኤል እንዳሉት፤ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ከተማዋን በኢንዱስትሪ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ተመራጭ እንድትሆን አድርገዋታል። 

በፅዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ ሁሉም ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እስከ መንደራቸው ያሉ አካባቢዎችን ጽዱና የተዋቡ በማድረግ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እያገዙ መሆኑን አስረድተዋል። 

በቀጣይም የኮሪደር ልማቱን ወደ ገጠር በማስፋት በከተማው እየመጣ ካለው ለውጥ ጋር በማስተሳሰር ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።


 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የምግብ ዋስትናና ሴፍትኔት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ዲባቤ በበኩላቸው፤ በከተማ ሴፍትኔት ፕሮግራም የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት አስችለዋል ብለዋል። 

በቀጣይም የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት በሚያሳድጉ የስራ ዘርፎች ላይ በማተኮር የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም