ቀጥታ፡

ምክክሩ ኢትዮጵያ የምትሻገርባቸውን የጋራ መፍትሔዎች ለማፈላለግ የሚያግዝ፤ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት ነው -ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያ የምትሻገርባቸውን የጋራ መፍትሔዎች ለማፈላለግ የሚያግዝ፤ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሂደቱን ገለልተኝነት፣አካታችነትና ተሳትፎ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ፤ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላም፣መግባባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጿል።

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው ጉባዔ፣ ኮሚሽኑ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ባዘጋጀው ዕቅድ መሠረት በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክቷል።

ምክክሩ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ጥልቅና ውስብስብ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተከፈተ ታሪካዊ ዕድል በመሆኑ፣ ሁሉም ወገኖች በባለቤትነት ሊንከባከቡት እንደሚገባ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ሂደቱን በነፃነት፣ በገለልተኝነት፣ በአካታችነት እና በአሳታፊነት ለማስኬድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝና የትኛውንም ልዩ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንዳልሆነ ገልጿል።

ኮሚሽኑ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በቅርቡ ያወጣውን መግለጫ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን፣ ሂደቱ አካታችና አሳታፊ አይደለም የሚለውን የአብን አቋም ተገቢውን ምርመራና ማጣራት ካደረገ በኋላ የማይጋራው መሆኑን አስታውቋል።

በምክክር ጉባዔው ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከተቋማትና ማህበራት፣ የመንግሥት አካላት፣ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን፣ የቀድሞ ታጣቂ ኃይሎች፣ የዳያስፖራው ማህበረሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወክለው የተለያዩ ድምፆች እየተሳተፉና እየተደመጡ እንደሚገኙና አብንም እስካሁን በሂደቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ካሉ ፓርቲዎች አንዱ መሆኑንም ነው የገለጸው።

ኮሚሽኑ የማንኛውንም ተመካካሪ አቤቱታና ቅሬታ በቀላሉ እንደማያልፈውና ለአብንም ሆነ ለሌሎች አካላት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች በቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ መሠረት ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ሂደቱን ለማሻሻል የሚቀርቡ ገንቢ አስተያየቶችና ቅሬታዎችን በግብዓትነት ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም አክሏል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ አብንንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በቀሪው የምክክር ሂደት በንቃት እንዲሳተፉ እና የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።

ሀገራዊ ምክክር የአንድ ወገን ድል ወይም የሌላ ወገን ሽንፈት አይደለም፡፡ኢትዮጵያ የምትሻገርባቸውን የጋራ መፍትሔዎች ለማፈላለግ የሚያግዝ፤ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት መሆኑንም ጠቅሷል።

ሀገራዊ ምክክር የአንድ ወገን ድል ወይም የሌላ ወገን ሽንፈት ሳይሆን ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት መሆኑን ጠቅሶ፣ የሁሉንም ዜጎች ድምፅ በእኩልነት ለማዳመጥና ሂደቱን በነፃነትና በገለልተኝነት ለመምራት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና ልዩ ልዩ ተቋማት ለምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርጉትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮሚሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል።

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!

ሀገራዊ ምክክር፤ ለሀገራዊ መግባባት!

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ነሐሴ 11 2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም