ቀጥታ፡

መንግስት ከዋናው የኤሌክትሪክ ሃይል መስመር ውጪ ባሉ አካባቢዎች የፀሐይ ኃይል ልማት ፕሮጀክቶችን በስፋት እየተገበረ ነው -የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር

ጭሮ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ) ፡-መንግስት ከዋናው የኤሌክትሪክ ሃይል መስመር ውጪ ባሉ አካባቢዎች የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎችን ለማስፋፋት የሚያደርገው ጥረት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን እያሳደገ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሐዊ ጉዲና ወረዳ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገለጸ።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)  ፕሮጀክቱን መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት፤ ከዋናው መስመር ውጪ የሚከናወኑ የኃይል ማዳረስ ሥራዎች የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን እያሳደጉት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሽፋን ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት 43 በመቶ ወደ 63 በመቶ ማደጉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ለዚህ እድገት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።


 

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሐዊ ጉዲና ወረዳ ተገንብተው ዛሬ የተመረቁት የሃሎ ጉባ፣ ቶርባን፣ ባቴ እና ሃሮ ኤባ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከ5 ሺህ በላይ ቤተሰቦችን የማገልገል አቅም ያላቸው ናቸው ብለዋል።

በገጠር አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎትን የማዳረስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ኅብረተሰቡም የተገነቡትን ፕሮጀክቶች የመጠበቅና የመንከባከብ ሀላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ ከበደ በበኩላቸው፣ በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በቅርቡ በዞኑ የአርብቶ አደር ወረዳ ሆና በተቋቋመችው ሐዊ ጉዲና ወረዳ የተገነባው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኅብረተሰቡን ሕይወት በመለወጥ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የወረዳው ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም ለወፍጮ አገልግሎት ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር ገልፀው አሁን ግን በመኖሪያ አከባቢዎቻቸው አገልግሎቱን ማግኘት በመቻላቸው ተደስተዋል።

በተለይም የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን በቤት ውስጥ ከመጠቀማቸው ባሻገር እስከ ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት ድረስ በመድረሱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተጠናቀው የተገነቡ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ931 ኪሎ ዋት በላይ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸው ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም