በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በየመስኩ ስኬታማ ስራዎችን ለማከናወን ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በየመስኩ ስኬታማ ስራዎችን ለማከናወን ተችሏል
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በማሕበራዊ እና ኢኮኖሚ መስኮች ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የ2018 በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ሪፖርትን አዳምጧል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ የነበሩ ፈተናዎችን በመቋቋም በግብርና፣ በማዕድን፣ በትምህርትና በሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል።
ከዚህ ውስጥም በ2017/18 የምርት ዘመን በመኸርና በበጋ መስኖ ልማት 229 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።
በቡና ልማት ዘርፍም በአርሶ አደሮችና በባለሀብቶች ከለማው 73 ሺህ 425 ሄክታር መሬት 53 ሺህ 756 ቶን ምርት መገኘቱን አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ በማዕድን ልማት ዘርፍ 6 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ 7 ሺህ 098 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማቅረብ መቻሉን ገልጸው አፈጻጸሙም ከእቅድ በላይ ነው ብለዋል።
የትምህርት ፍትሐዊነትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎችም በአንደኛ፣ በመካከለኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 157 ሺህ ተማሪዎችን የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
በጤና፣ በንጹሕ መጠጥ ውሃ እና በሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የነበሩትን ፈተናዎች በመቋቋም በበጀት ዓመቱ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን በሪፖርቱ ጠቁመዋል።