ቀጥታ፡

በፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር ቅንጅታዊ ሥራዎች ቀጥለዋል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ) ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ ሥራዎች መቀጠላቸውን የክልሉ ርዕሰመስተዳደር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ።

"ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ለ3ኛ ዙር የተዘጋጀ የፅዱ ኢትዮጵያ የንቅናቄና የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ እንዳሉት በክልሉ በፅዱ ኢትዮጵያ ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ ሥራዎች ቀጥለዋል።

ንቅናቄው ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር እያገዘ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በቀጣይም ህዝቡን ባለቤት በማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።

ለዚህም ጽዳትን ባህሉ ያደረጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የአመራሩንና የባለድርሻ አካላትን ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው እንዳሉት በመደመር መንግስት እሳቤ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በጋራ በማከናወን ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።


 

የጽዱ ኢትዮጵያ ቀጣይ 3 ወራት ንቅናቄም ፕላስቲክን በአግባቡ የመጠቀም፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የፋብሪካ ኬሚካሎች አወጋገድና የድምጽ ብክለትን መከላከል ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ለተተኪው ትውልድ ጤናማና ምቹ አካባቢን ለማስተላለፍ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሚጠናከሩም አክለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አብርሃም መጫ እንደገለጹት በክልሉ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ትግበራ የተራቆተ መሬትን በማልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስችሏል።


 

ከዚህ በተጨማሪ የከተሞችን ውበት ማስጠበቅን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ቢሮው በቀጣይ 3 ወራት በሚተገበረው የፅዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።


 

በመድረኩ የክልሉ፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና ተጋባዥ እንግዶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም