ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የዳኝነት እና የፍትህ ስርዓቱን ለማዘመን የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ ነው

አዳማ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፡-የፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት የፍትህና የዳኝነት ስርዓቱን ለማዘመን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገለፀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዘካርያስ ኤርኮላ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት በሀገር ደረጃ እየተተገበረ ያለው የፍትህ ሪፎርሙ ውጤታማ እንዲሆን በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና አሰራርን በማዘመን ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይም የዳኝነትና የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን፣ የህግና ፍትህ መረጃዎች አደረጃጀትና አያያዝን፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የዲጂታል አሰራር ስርዓት አተገባበርና ተደራሽነትን በተመለከተ የጥናትና ምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከምርመራ ጀምሮ እስከ ዐቃቤ ህግ፣ ፍርድ ቤትና ማረሚያ ቤት ድረስ ባለው አሰራር መካከል የተናበበና ወጥ የሆነ የፍትህ ስርዓት ለማረጋገጥ፣ በዲጂታላይዜሽን አሰራር ውጤታማነት ላይም በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የፍትህ ስርዓቱን የአሰራር ማሻሻያ ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የዕውቀትና ክህሎት የአቅም ግንባታ ስራዎች በቴክኖሎጂ  የተደገፉ እንዲሆኑ እያደረግን ነው ብለዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ እንደገለጹት፣ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን አሰራር ዲጂታል ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

"ውጤታማና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት ዲጂታላይዜሽን ወሳኝ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ተገልጋዮች ሳይንገላቱና ለወጪ ሳይዳረጉ ባሉበት ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ የፍርድ ቤቶች አሰራሮች ዲጂታል እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በተለይም በሰበር ሰሚ ችሎት የቪዲዮ ኮንፈረንስን ተግባራዊ በማድረግ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው ውሳኔ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ወደ ዲጂታል አሰራር በሙሉ አቅም ለመግባት መረጃዎችን በቴክኖሎጂ የማደራጀትና በሲስተም ውስጥ የማስቀመጥ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በአዳዲስ አሰራሮች፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በሰው ሃይል አቅም ግንባታ ላይ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በትብብር እያከናወኑ ያሉትን ተግባራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሽተባ አባድር በበኩላቸው፣ የፍትህ ሪፎርሙን ውጤታማና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ግብ ለማሳካት የፍትህ ተቋማትን አገልግሎት የማዘመን ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዳኝነትና በፍትህ ዘርፍ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስና ዘመናዊ አሰራሮችን እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣ ኢንስቲትዩቱ የህግ ጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ለፍትህ ሪፎርሙ ስኬት የሚያግዙ ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ጋር በአሰራር፣ በክህሎት ማደራጃ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በአቅም ግንባታ ላይ በትብብር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በክልሉ የበይነ-መረብ የህግ ክርክር ለማስጀመር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የዲጂታል አሰራር ዝርጋታን በማጠናቀቅ አገልግሎቱን ወደ ስራ ለማስገባት መሆኑን አክለዋል።


 

የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አኢሻ ሚኔ እንደገለጹት፣ የዳኝነትና የፍትህ አገልግሎቱን ለማዘመን መዝገቦችን ስካን በማድረግ የዲጂታል አገልግሎት የመስጠት ተግባር እየተከናወነ ነው።

በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በሰበር ሰሚ ችሎቶች የስማርት ችሎት አገልግሎት ማስጀመር መቻላቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፣ በዚህም የውሳኔ ግልባጭና ይግባኞችን ከወረቀት ንክኪ ነፃ በማድረግ ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተችሏል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የበይነ-መረብ ትምህርትና ስልጠናውን ለማስጀመር የተዘጋጁ ኮርሶችንና ሞጁሎችን በየደረጃው ለሚገኙ የፌዴራልና የክልል የፍትህ ሴክተር አመራሮች እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት የማስተዋወቅና ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዳማ ማካሄዱ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም