እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ጉባኤ በየቡድኖች የተጠናቀሩ ምክረ ሃሳቦችን የማጣጣም ሥራ እየተጠናቀቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ጉባኤ በየቡድኖች የተጠናቀሩ ምክረ ሃሳቦችን የማጣጣም ሥራ እየተጠናቀቀ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦ እየተካሄደ በሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በየቡድኖቹ የተጠናቀሩ ምክረ ሃሳቦችን የማጣጣም ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ስላሴ እየተካሄደ የሚገኘውን ምክክር አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ከስምንቱ ቡድኖች የተውጣጡ 120 የሚጠጉ ተወካዮች ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ ምክረ ሃሳቦችን የማጣጣም ስራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከየቡድኑ የተወጣጡት 15 ተወካዮች፣ በስምንቱ ቡድኖች መካከል የተዘጋጁ ምክረ ሃሳቦች ድግግሞሽ እንዳይኖርባቸው፣ በአንድ ወጥ መልክ እንዲቀርቡ የማጣጣም ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።
ተወካዮቹ ስለሌሎች ቡድኖች ምክረ ሃሳቦችም ግንዛቤ በመውሰድ እርስ በርስ የሚመካከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተጣጣሙት ምክረ ሃሳቦች ለስምንቱም ቡድኖች ተመልሰው እንደሚቀርቡ ጠቅሰው፣ ቡድኖቹም ዛሬ ከሰዓት በኋላ በተሰራው ስራ ላይ ግብዓት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የተሰበሰበው ግብዓት ነገ ላይ ተጠናቅሮ፣ ረቡዕ ዕለት በአራትሺህ ተሳታፊዎች እንደሚጸድቅ አብራርተዋል።