የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ
ባህር ዳር፤ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ደረጃቸውን የጠበቁ መማሪያ ክፍሎችን በመገንባት የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየርና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለፁ።
በባህር ዳር ከተማ በከተሞች የምግብ ዋስትናና ሴፍትኔት ፕሮግራም ደረጃቸውን ጠብቀው የተገነቡ መማሪያ ክፍሎችና የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምረቃ ሥነ ስርዓት ተካሄዷል።
የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የትምህርት ቤቶችን የተጎሳቆለ ገፅታ በመቀየር ፅዱ፣ ውብና አረንጓዴ የለበሱ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው።
ለእዚህም የከተማዋን ገጽታ በሚመጥን አግባብ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዚህም በከተማው ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ፣ ጽዱና ውብ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር እያሳደገ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ትምህርት ላይ የሚሰሩ የልማት ሥራዎች ለሃገሩና ለወገኑ ርዕይ ያለው ትውልድ ብሎም ለሃገሩ ልማትና ብልፅግና የሚተጋ ብቁ ዜጋ የማፍራት ሥራን ያጠናክራሉ ብለዋል።
ተወዳዳሪና የበቃ ዜጋ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ከትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻልና ከትምህርት ጥራት መረጋገጥ ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደሆነም ገልፀዋል።
በመሆኑም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ በቴክኖሎጂ ለማደረጃት የተጀመሩ ስራዎች ይበለጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አረጋግጠዋል።
በዛሬው እለትም በአምስት ሕንጻዎች የተገነቡ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 20 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የከተሞች ምግብ ዋስትናና ሴፍትኔት ፕሮግራም የከተሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ማቃለል ያስቻለ ነው።
በክልሉ በተመረጡ 18 ከተሞች ከ600 ሺህ በላይ ወገኖች በፕሮግራሙ ታቅፈው ተጠቃሚ እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በፕሮግራሙም በርካታ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በፕሮግራሙ የታቀፉ ወገኖችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ ለህዝብ ግልጋሎት የሚውሉ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመገንባት የተሻለ ሥራ ተሰርቷል።
የመማር ማስተማር ሥራውን ለማገዝ በተደረገ ጥረትም 73 ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ተገንብተው ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
በቀጣይም በፕሮግራሙ የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።