ቀጥታ፡

በኢሉባቦር ዞን በኩታ ገጠም ከለማው የበቆሎ ሰብል የተሻለ ምርት ለማገኘት የእንክብካቤ ስራ ተጠናክሯል

መቱ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በኢሉባቦር ዞን በክረምት እርሻ እየለማ ከሚገኘው የበቆሎ ሰብል የላቀ ምርት ለማገኘት የሰብል እንክብካቤና ጥበቃ ስራ በተቀናጀ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።

የኦሮሚያ ክልል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ምርታማነትን ለማሳደግ የ"ኩታ ገጠም" የእርሻ ዘይቤን በስፋት በመተግበር ላይ ይገኛል።

በክልሉ በክረምት ወቅት እንደ በቆሎ፣ ስንዴ፣ እና ጤፍ ያሉ ዋና ዋና ሰብሎች በስፋት ይመረታሉ።

በቆሎ ለሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት መኖ እና ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነት ከፍተኛ ሚና ስላለው፣ በዘመናዊ አሰራር እና በኩታ ገጠም ዘዴ ምርታማነቱን ማሳደግ የክልሉ ዋና የልማት ግብ ነው።

ከኦሮሚያ ክልል ዞኖች አንዱ የሆነው ኢሉባቦር ዞን በተለይም ለጥራጥሬ እና ለበቆሎ ሰብል ልማት እጅግ ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው በመሆኑ፣ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች በክረምት ወቅት በቆሎን በስፋት ያመርታሉ።

በዚሁ መሰረት በዞኑ በሁሩሙ ወረዳ በኩታ ገጠም የበቆሎ ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች እንደገለጹት፣ የታቀደውን ከፍተኛ ምርት ለማሳካት አረም የማረም፣ ኩትኳቶና የሰብል ጥበቃ ስራዎችን በትኩረት ያከናውናሉ።

በዞኑ የሁሩሙ ወረዳ አርሶ አደር መብሬ አለነ እንደተናገሩት፤ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት በቆሎን በኩታ ገጠም እያለሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለሰብሉ የሚያደርጉት ጥንቃቄና እንክብካቤ አሁን ላይ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንዲገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል።

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ይመር ከበደ በበኩላቸው መሬት ማረስና ዘር መዝራት ብቻ በራሱ ለውጤት እንደማያበቃ ተናግረው፤ በዚህም የሰብል ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በባለሙያ እገዛ በኩታ ገጠም ከለማው ማሳቸው የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ የሰብል እንክብካቤና ጥበቃ ስራውን ቤተሰቦቻቸውን በማሳተፍ በትጋት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኜ ፍቅሬ እንደገለጹት፤ በዞኑ በክረምቱ ወቅት ከ389 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 95 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በበቆሎ ሰብል የተሸፈነ ነው።

በልማቱ ውጤታማ እንዲሆኑ ለአርሶ አደሮቹ የግንዛቤ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በበቆሎ ሰብል ከተሸፈነው 95 ሺህ ሄክታር መሬት የታቀደውን 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት ስብሰባ ባለው ሂደት አርሶ አደሩ የሰብል ጥበቃ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ እንዲያከናውን እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በአጠቃላይ የክረምት እርሻ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ ሙያዊ ድጋፍና የክትትል ሰራዎች  ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አብራርተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም