ቀጥታ፡

የፀሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ ለረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄያችን ምላሽ የሰጠ ነው- የቁምቢ ወረዳ ነዋሪዎች

ቁምቢ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦ የፀሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ ለረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄያችን ምላሽ የሰጠ ነው ሲሉ በምስራቅ ሐረርጌ ተናገሩ።

በወረዳው ሀሮ ጉራቲ እና ሀሪሮ ቀበሌዎች በ640 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሰሞኑን ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።
    
ፕሮጀክቶቹ ተመርቀው አገልገሎት መጀመራቸው በአካባቢው በተደጋጋሚ የነበረውን የሃይል መሰረተ ልማት ጥያቄ መሰረት ያደረገ ሲሆን ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በቁምቢ ወረዳ የሃሪሮ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል መምህር ማዕሩፍ አብደላ እና ወይዘሮሂ ክማ  ቀመር፤ የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ለአገልግሎትና የልማት ስራዎች ጭምር ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል።

በመሆኑም የኃይል ልማት የማህበረሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ እንደነበር አስታውሰው፤ ምላሽ በማግኘቱና መሰረተ ልማቱ በመሟላቱ ተደስተናል ብለዋል።

የፀሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ ለረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄያችን ምላሽ የሰጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የፀሐይ ኃይል አገልግሎት በመጀመሩ በተለይም ለትምህርት ተቋማት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ያነሱት መምህር ማዕሩፍ፤ ለተሻለ የትምህርት አሰጣጥና ተደራሽነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአካባቢያቸው የፀሐይ ኃይል አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ ግን በዳቦ በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ያነሱት ደግሞ የቀበሌው ተወላጅ ወይዘሮሂ ክማ  ቀመር ናቸው።

በመሆኑም በተሰማሩበት የምግብ ቤትና የዳቦ የማምረት ስራ ውጤታማ ለመሆን በትጋት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የሐሪሮ ሆስፒታል ጠቅላላ ሀኪም ዶክተር አፈንዲ አልይ፤ በአካባቢው የሃይል መሰረተ ልማት ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ በተለይም ለማህበራዊ አገልገሎትና አጠቃላይ ለኢኮኖሚ ልማት ብዙ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል።

ለአብነትም ሆስፒታሉ ቀደም ሲል ውስን ሰዓት የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ወደ 24 ሰዓት እንዲያድግ እንዲሁም የላብራቶሪና የራጅ አገልግሎት በተሻለ መልኩ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ (ዶ/ር)፤ በተለይ በተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር፣በንጹህ መጠጥና ሳኒዬሽና በሃይል አቅርቦት በተከናወነው ተግባራት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የተመረቁት የኃይል ልማት ፕሮጀክቶች በድምሩ 900 ኪሎ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸውና ከ4 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም