ካሜሮን ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫን አነሳች - ኢዜአ አማርኛ
ካሜሮን ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫን አነሳች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በ14ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ካሜሮን ማላዊን 3 ለ 0 አሸንፋለች።
ማምሻውን በሞሮኮ ራባት በሚገኘው የሙላይ አል ሀሰን ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ካሜሮን ፍጹም የበላይነትን ወስዳለች።
ማሪ ንጋህ በ20ኛው እና በ45ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ ስታሳርፍ፣ ናኦሚ ንጆአ ኤቶ በ30ኛው ደቂቃ ላይ ሶስተኛዋን ግብ አክላለች።
ማላዊ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ብታደርግም የካሜሩንን የተከላካይ ክፍል ሰብራ ግብ ማስቆጠር አልቻለችም።
ካሜሮን ውጤቱን ተከትሎ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ አንስታለች።
የማይበገሩት አንበሶች ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሰው ማሸነፍ አልቻሉም ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ የቀረበችው ማላዊ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ይህ ድል ለካሜሩን የዋንጫ ክብር ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማትንም ያስገኘ ነው።
አሸናፊዋ ካሜሩን ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የሁለት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ሽልማት የምታገኝ ሲሆን፣ ይህ ስኬት ቡድኑን በቀጥታ እ.አ.አ በ2027 በብራዚል ለሚካሄደው 10ኛው የፊፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ያረጋገጠላት ሆኗል።
ከካሜሩን በተጨማሪ ግማሽ ፍጻሜ የደረሱት ማላዊ፣ ሞሮኮ እና ናይጄሪያም አፍሪካን ወክለው በዚህ ታሪካዊ የዓለም ዋንጫ ላይ ይሳተፋሉ።
ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ማላዊ የ750 ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከትላታል።
አዘጋጇን ሞሮኮን በደረጃ ጨዋታ በመለያ ምት በመርታት ሶስተኛ የወጣችው አልጄሪያ የ550 ሺህ ዶላር ሽልማት ታገኛለች።
ሞሮኮ የ300 ሺህ ዶላር ሽልማት ወደ ካዝናዋ ታስገባለች።
ሞኒክ ንጎክ (ካሜሩን) የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመር ጣለች።
ሚካኤሊ ቢሂና (ካሜሩን) በውድድሩ ላይ ባሳየችው ብቃት ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆናለች።
ቴምዋ ቻዊንጋ (ማላዊ) አምስት ግቦችን በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢነቱን የወርቅ ጫማ ወስዳለች።
ከሰኔ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሞሮኮ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ 12 ሀገራት ተሳትፈውበታል።