በተቀናጀ ዐቅም ተግተን ከሠራን ብልጽግና ሕይወት፣ድህነት ታሪክ ይሆናል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በተቀናጀ ዐቅም ተግተን ከሠራን ብልጽግና ሕይወት፣ድህነት ታሪክ ይሆናል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ ፤ነሀሴ 10 /2018 (ኢዜአ)፦ለም አፈር፣ ንጹሕ ውኃና ሥራ ወዳድ ሕዝብ ባለበት ምድር፣ በተቀናጀ ዐቅም ተግተን ከሠራን ብልጽግና ሕይወት፣ ድህነት ታሪክ ይሆናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት የሃይቅ ዙሪያ አርሷደሮች መሬት እና እርሻቸውን ከጫት ወደ አትክልት እና ፍራፍሬ ክላስተር አሸጋግረውታል ብለዋል።
አርሷደሮቹ የአካባቢን አንጻራዊ የልማት ጉልበት መለየት እና ወደ አትራፊ እና ዘላቂ የግብርና ጎዳና መሸጋገር ይገባል የሚለውን ሃገራዊ መርህ እና ስምሪት ተግብረው አሳይተዋል ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ምርቃት ላይ ባስተላለፉት ታሪካዊ መልዕክት "ሐይቅ የታሪክ ብቻ ሳይሆን የፍራፍሬ ልማት፣ የተትረፈረፈ ምርት፣ የውበትና የጥጋብ ሥፍራ መሆን አለባት" ማለታቸውን አስታውሰዋል።
ዛሬ የርሳቸው ቃል ፍሬ አፍርቶ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን፣ ተሁለደሬ ወረዳ የጎበያ ቀበሌ በአትክልት እና ፍራፍሬ ክላስተር ተሸፍኗል። ይህ የልማት ትጋት ኢትዮጵያ ለጀመረችው የምግብ ሉዓላዊነት ተደማሪ ጥሪት እና ወረት ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
መንግሥት ለዚህ ልማት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ያሉ ሲሆን ለም አፈር፣ ንጹሕ ውኃና ሥራ ወዳድ ሕዝብ ባለበት ምድር፣ በተቀናጀ ዐቅም ተግተን ከሠራን - ብልጽግና ሕይወት፣ ድህነት ታሪክ እንደሚሆን ገልጸዋል።