ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን በህፃናትና ታዳጊዎች ላይ መስራት የነገዋን ኢትዮጵያ መገንባት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል

ዲላ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- መገናኛ ብዙሃን በህፃናትና ታዳጊዎች ላይ መስራት የነገዋን ኢትዮጵያ መገንባት መሆኑን በመገንዘብ ለተግባሩ ትኩረት እንዲሰጡ ተመላከተ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በጌዴኦ ዞን ወናጎ ከተማ በሌ ቡቂሳ ትምህርት ቤት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀምሯል።


 

ባለሥልጣኑ ከግንባታው ማስጀመር ጎን ለጎንም በወናጎ ከተማ ለሚገኙ 300 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉም ተመልክቷል። 

የባለሥልጣኑ ተወካይና የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስራቅ ጌቱ በወቅቱ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ ለእውነተኛ መረጃ ተደራሽነት ድጋፍና ክትትል ከማድረግ ባለፈ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው። 

ዛሬ በጌዴኦ ዞን ወናጎ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በማስገንባት ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ትምህርት ቤቱን ለአዲሱ ትምህርት ዘመን ለማድረስ እንደሚሰራ ጠቅሰው ይህም ለተማሪዎች ምቹ የትምህርት ከባቢን በመፍጠር የመማር ማስተማር ሂደትን ለማሳለጥ እንደሚያስችል አስረድተዋል። 

ባለሥልጣኑ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ማስጀመር ጎን ለጎን በወናጎ ከተማ ለሚገኙ 300 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። 


 

ህፃናትና ታዳጊዎች ላይ መስራት የነገዋ ኢትዮጵያን መገንባት በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን በዚህ ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል። 

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር ) ባለስልጣኑ በዞኑ የሚያስገነባው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያጠናክር ነው ብለዋል። 


 

በተያዘው በጀት ዓመትም በዞኑ 18 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን አንሰተው የዛሬውም ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። 

የወናጎ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በበኩላቸው ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱን ግንባታ በአጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅም ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።


 

የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም በመማርያ ግብዓቶች እጥረት አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆን ድርሻው የጎላ ነው ብለው ለድጋፉ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም