በሀዋሳ ከተማ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል--ከንቲባ ጥራቱ በየነ - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ከተማ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል--ከንቲባ ጥራቱ በየነ
ሀዋሳ፤ ነሀሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- በሀዋሳ ከተማ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቸ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን የከተማዋ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ።
“ኮሪደር ልማት ለስፖርት ቱሪዝም” በሚል መሪ ሀሳብ የታዳጊዎችና ወጣቶች የፕሮጀክት ስፖርታዊ ውድድር በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እንዳሉት፣ ወጣቶችና ሕጻናት በስፖርቱ ዘርፍ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ የነገ ተተኪ ስፖርተኞች እንዲሆኑ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በከተማዋ የሚካሄዱ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ወጣቶችን፣ ሕጻናትንና አረጋውያንን ታሳቢ ያደረጉ ምቹ የመዝናኛ፣ የማረፊያና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ያካተቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በስፖርቱ ዘርፍ ሀዋሳ ከተማን፣ የሲዳማ ክልልንና ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት በአራት ዙር በተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች 15 የሕጻናት መጫወቻ፣ የወጣቶችና ታዳጊዎች ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታዎች በዕቅድ መካተታቸውን አብራርተዋል።
ከነዚህም ሦስት የታዳጊዎችና ሦስት የወጣቶች (በጠቅላላው ስድስት) ሰው ሰራሽ ሣር የተነጠፈላቸው የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ 4 የቅርጫት ኳስ ሜዳዎች፣ 5 የሕጻናት መጫወቻ ስፍራዎችና የሜዳ ቴኒስ ማዘውተሪያዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን አመልክተዋል።
አቶ ጥራቱ አክለውም፤ ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን በአልባሌ ስፍራ ከማሳለፍ በመራቅ በስፖርት ላይ እንዲያተኩሩና እነዚህን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በአግባቡና በጥንቃቄ እንዲይዟቸው አሳስበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ በላይነሽ ገዳ በበኩላቸው፣ በከተማዋ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ለአምስት ቀናት የሚቆይና በእግር ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በብስክሌትና በሜዳ ቴኒስ በሁለቱም ጾታዎች 34 ቡድኖች የሚሳተፉበት የፕሮጀክቶች ስፖርታዊ ውድድር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ለዘርፉ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የገለፁት ደግሞ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዶማርሶ ዶና ናቸው።
በፕሮጀክት ውድድሩ ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ስፖርተኞች መካከል ወጣት ፍላጎት ተሻ እና ወጣት ሚካኤል ፍጹም እንደገለጹት፣ በከተማዋ የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ባላቸው ፍላጎትና ተሰጥኦ መሠረት እንዲሳተፉ አስችሏቸዋል።
በክረምቱ ወቅት በተለያዩ መስኮች በፕሮጀክት ታቅፈው ሲሰለጥኑ መቆየታቸው ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ላይ እንዳያባክኑ ትልቅ እድል እንደፈጠረላቸውም አክለዋል።
በስነ-ሥርዓቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩና የክልሉ አመራሮች እንዲሁም ወጣቶች ተገኝተዋል።