አርሰናል ማንችስተር ሲቲን 3 ለ 0 በማሸነፍ የኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫን ለ18ኛ ጊዜ አነሳ - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ማንችስተር ሲቲን 3 ለ 0 በማሸነፍ የኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫን ለ18ኛ ጊዜ አነሳ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ):- አርሰናል ማንችስተር ሲቲን 3 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ የ2026 የኤፍኤ ኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫን ለ18ኛ ጊዜ አሳክቷል።
በዌልስ መዲና ካርዲፍ በሚገኘው ታሪካዊው ፕሪንሲፓሊቲ ስታዲየም በተካሄደው የውድድር ዘመን መክፈቻ ጨዋታ፤አርሰናል በጨዋታው ላይ ፍጹም የበላይነት በመውሰድ ነው ማንችስተር ሲቲን ማሸነፍ የቻለው።
ለአርሰናል የማሸነፊያ ግቦቹን ተከላካዩ ሪካርዶ ካላፊዮሪ፣ አጥቂው ካይ ሃቨርትዝ እና የቡድኑ አንበል ማርቲን ኦዲጋርድ አስቆጥረዋል።
ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ክብር የተቀዳጀው አርሰናል እና በኤፍኤ ካፕ ፍፃሜ ቼልሲን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለዚህ ጨዋታ የበቃው ማንቸስተር ሲቲ ያደረጉት ይህ ጨዋታ፤ አርሰናል በኮሙኒቲ ሺልድ መድረክ በማንቸስተር ሲቲ ላይ ያለውን ፍጹም የበላይነት አስቀጥሏል።
ሁለቱ ቡድኖች በዚሁ መድረክ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች በሙሉ አርሰናል ያሸነፈ ሲሆን፣ የዛሬው ድል በዚሁ መድረክ በማንቸስተር ሲቲ ላይ ያስመዘገበውን አራተኛ ተከታታይ ድል አድርጎታል።
አርሰናል የዋንጫ ቁጥሩን ወደ 18 በማሳደግ በውድድሩ ታሪክ 21 ዋንጫዎችን በማንሳት የመጀመሪያውን ደረጃ ከያዘው ማንቸስተር ዩናይትድ ቀጥሎ ያለውን ስኬታማነት አጠናክሯል።