ቀጥታ፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ (ጋሽ ደቤ) ለሙያው የነበረው ጥልቅ ፍቅርና ትጋት ለትውልድ የሚሻገር የጥበብ ዐሻራ ጥሎ እንዲያልፍ አስችሎታል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፦አንጋፋው የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱ (ጋሽ ደቤ) ለሙያው የነበረው ፍቅርና ትጋት ለትውልድ የሚሻገር ዐሻራ ጥሎ እንዲያልፍ ማስቻሉን የተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ተሾመ ፈይሳ ገለጹ።

የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለኢትዮጵያና አፍሪካ የቴአትር ጥበብ ዘመናዊነት የላቀ አሻራ ያሳረፉት ታላቁ የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱ (ጋሽ ደቤ) የአንደኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ አካሂዷል።


 

ኮሌጁ ባዘጋጀው የሙት ዓመት መታሰቢያ በአንጋፋው የጥበብ ሰው ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ ስም የቴአትር ማሰልጠኛ መድረክ  ሰይሟል።

መርሃ ግብሩ ታላቁ አርቲስት ደበበ እሸቱ (ጋሽ ደቤ) በሕይወት ዘመኑ ለሀገር፣ ለሕዝብና ለጥበብ ያበረከተውን የላቀ አስተዋጽኦ ለመዘከርና ያሳረፈውን አሻራ ለማስታወስ የተዘጋጀ ነው።

የተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ተሾመ ፈይሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አርቲስቱ የተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅን የትምህርት ጥራትና የሙያ ክብር ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

አንጋፋው የባለብዙ ተሰጥኦ ባለቤት አርቲስት ጋሽ ደቤ ለሙያው በነበረው ፍቅርና ትጋት ለትውልዱ አርአያ ሆኗል ብለዋል።

ኮሌጁም የአርቲስቱን ፈለግ በመከተል ትውልዱን በጥበብና በሙያ ለመቅረጽ ዓላማ አንግቦ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

አርቲስቱ ለሀገር ብሎም ለኮሌጁ ባበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የኮሌጁ የቴአትር ማሰልጠኛ መድረክ በክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ ስም መሰየሙን ተገልጿል።


 

የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪ ካፒቴን ከበደ ወልደፃዲቅ፤ አርቲስቱ ባለብዙ ተሰጥኦ የጥበብ ሰው በመሆን ከሀገር ውስጥ መድረኮች ባሻገር በአፍሪካ የቴአትር መድረክ ላይ አመራር የሰጠ እንደነበር ተናግረዋል።

በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የተጀመረውን የጥበብ ጉዞ በውጭ ሀገር ካገኘው የቴአትር ትምህርት ጋር በማቀናጀት ለሀገሩ የኪነ-ጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል።

የደበበ የጥበብ ጉዞ የአንድ አርቲስት ታሪክ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የዘመናዊ የስነ-ጥበብ ታሪክ አንድ ክፍል መሆኑንም ተናግረዋል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ከነበረው ጥልቅ የጥበብ ፍቅር ባሻገር እስከ ሕይወት ፍጻሜው ድረስ የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር የቦርድ አባል በመሆን ለተቋሙ አርአያ የሚሆን ተግባር ማከናወኑንም ጠቅሰዋል።


 

የአርቲስት ደበበ እሸቱ (ጋሽ ደቤ) ባለቤት ወይዘሮ አልማዝ ደጀኔ እንዳሉት፤ የአርቲስት ደበበ እሸቱ ዐሻራ በመድረክ ላይ ብቻ የቀረ ሳይሆን በተማሪዎች፣ በባልደረቦችና በአድናቂዎቻቸው ልብ የቀጠለ ነው።

ለታላቁ አርቲስት ደበበ እሸቱ በተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአንደኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር በማዘጋጀቱ ምስጋና አቅርበዋል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የቴአትርና የፊልም ታሪክ ውስጥ ታላቅ ዐሻራ ጥሎ ያለፈ ሁለገብ አርቲስት ነው።

ከ40 በላይ የመድረክ ተውኔቶችና በርካታ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል ፊልሞች ላይ በተዋናይነት፣ በዳይሬክተርነትና በተርጓሚነት ተሳትፏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም