በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞችን በፕላን ለመምራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው-ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞችን በፕላን ለመምራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው-ኢንስቲትዩቱ
ጎንደር ፤ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞችን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል ፕላን ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ፕላን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ያለፈው ዓመት አፈጻጸም፣ የ2019 ዕቅድ ትውውቅና የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን መሠረት ያደረገ የውይይት መድረክ በጎንደር ከተማ እያካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ተስፋሁን ተናኜ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ፣ ተወዳዳሪና ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው።
ከዚህ ውስጥም የከተሞችን ዕድገት ለማፋጠን በየደረጃው መዋቅራዊ ፕላን በማዘጋጀት እስካሁን ከ137 በላይ ለሚሆኑ ከተሞች የፕላን ዝግጅት ተከናውኗል።
በተጨማሪም፣ ከ31 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የግንባታ ጥያቄዎች በከተሞች ፕላን መሠረት መከናወናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
ይህም በከተሞች የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራትና ቴሌኮም የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲሳለጡ የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመትም የተጀመሩ ተግባራትን በማጠናከር፣ የከተሞችን ዕድገትና ዘመናዊነት የሚያረጋግጡ ዕቅዶች ተግባራዊ ይደረጋሉ ነው ያሉት።
በክልሉ ፕላን ኢንስቲትዩት የጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው አዳነ በበኩላቸው፣ የከተሞች ፕላን ክለሳ፣ የመዋቅራዊና መሠረታዊ ፕላን ዝግጅት እና የሰፈር ልማት ፕላን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ሥር የሚገኙ ከተሞችን በመከታተል የፕላን ዝግጅትና ትግበራ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚካሄደው በዚህ መድረክ ላይ የኢንስቲትዩቱ የሥራ ኃላፊዎችና የቅርንጫፍ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።