የምክክር ጉባኤው መግባባት የሰፈነባትና ብሩህ ተስፋ ያላትን ሀገር እንደሚፈጥር ጽኑ እምነት አለን-ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው መግባባት የሰፈነባትና ብሩህ ተስፋ ያላትን ሀገር እንደሚፈጥር ጽኑ እምነት አለን-ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፦የኢትጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መግባባት የሰፈነባትና ብሩህ ተስፋ ያላትን ሀገር እንደሚፈጥር ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተመካካሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።
ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
በምክክሩ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንቱ ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ እየደረሱ ይገኛሉ።
ተመካካሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምክክር ጉባኤው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት መሠረት የሚጥሉ የጋራ መግባባት ምክረ ሀሳቦች የሚፈልቁበት የሚፈልቁበት ነው።
በሂደቱ የሚደረሱት ስምምነቶችም ሕብረብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን በባለቤትነት መንፈስ የሀገራቸውን የነገ ብሩህ ዕጣ ፈንታ እንዲወስኑ እና ሀገራዊ መግባባት የሰፈነባትን ሀገር መገንባት የሚያስችል ታሪካዊ መሰረት እንደሚጥል ገልጸዋል።
ተመካካሪና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር)፤ በምክክር ጉባኤው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እኩል የሚሳተፉበት አካታችና አሳታፊ የጋራ መድረክ ነው ብለዋል።
ተመካካሪዎች ከ10 እስከ 500 በሚደርሱ የቡድን አደረጃጀቶች የሚመካከሩባቸው ዕድሎች መፈጠራቸው ሃሳብን በነፃነት በማንጸባረቅ አሳታፊ የምክክር ምህዳር እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።
ሂደቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አብሮነት መሠረት የሚጥሉ የጋራ መግባባት ምክረ ሀሳቦች የሚፈልቁበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላኛው ተመካካሪና የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ቦርድ አባል ኢንጂነር አለማየሁ ንጋቱ በበኩላቸው፤ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ ችግሮችን በሰለጠነ ምክክር በመፍታት መግባባት የሰፈነባትና ብሩህ ተስፋ ያላትን ሀገር እንደሚፈጥር ጽኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ህዝብ ለልማት በጋራ የሚነሳበት አውድ በመፍጠርም የተረጋጋች እና ዘላቂ ሰላም ያላት ሀገር ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋምን በመወከል እየተመካከሩ የሚገኙት አብዲሳ አበበ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በምክክሩ ሁሉም የሕዝብ ወኪል ሃሳቡን በነፃነት እያቀረበበት ይገኛል።
የተለያዩ ሃሳቦች ያለ ገደብ እንዲነሱ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው፤ ይህም ችግሮችን አሳታፊ በሆነ መንገድ በመመካከር ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ የሚበጁ መፍትሄዎችን ማምጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በተመካካሪዎች እየተነሱ ያሉት ሀሳቦች ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ ሰላም፣ከፍታና እድገት ለማሻገር እንደሚያግዝ ገልፀው፤ሂደቱ ለሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።