የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተተገበሩ የፖሊሲ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው - ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተተገበሩ የፖሊሲ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው - ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፦የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተተገበሩ የፖሊሲ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማሳደግ ተግባራዊ የተደረጉ የፖሊሲ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤቶች እያመጡ ነው።
የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል የተመቻቹ የፋይናንስ አቅርቦት ዕድሎች የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ እያሳደጉ መምጣታቸውንም ገልጸዋል።
ይህም የግሉ ዘርፍ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች የትብብር መስኮች የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማጎልበት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችና ሜካናይዜሽን በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደላድል በመፈጠሩም የምርት መጠንና ጥራት እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥም በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ያለውን ጥገኝነት በሀገር ውስጥ አቅም ለመተካት የሚያስችል የማዳበሪያ ፋብሪካ በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑን አንስተዋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአምስት ዓመታት ጊዜ የታረሰውን መሬት በሦስት እጥፍ ማሳደግ እንደተቻለ አስረድተዋል።
በዚህም በሰብልና በእንስሳት ሃብት ልማት ምርታማነትን ጨምሮ በሁሉም የግብርና ዘርፎች የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እምርታዊ ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥም ከሀገር ነፃነትና ደህንነት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቀነስ ለግብርና ምርታማነት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው ብለዋል።
ይህም የግብርናውን ትራንስፎርሜሽን ውጤታማነት በማጎልበት የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ መሠረት ከመጣል ባሻገር በሥራ ዕድል ፈጠራም የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች እየተገኙበት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የውጭ ምንዛሬ ግኝትም እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አረንጓዴ ዐሻራ የሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን በማስጠበቅ በካርቦን ሽያጭ ጭምር ገቢ መፍጠር እያስቻለ ነው ብለዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ሥርዓት ለመገንባት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።