ቀጥታ፡

ምክክሩ የጋራ መግባባትን የሚገነቡ አካታችና አሳታፊ ሃሳቦች የተንጸባረቁበት ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፦በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የጋራ መግባባትን የሚገነቡ አካታችና አሳታፊ ሃሳቦች በነጻነት የተንጸባረቁበት መሆኑን ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

በምክክሩ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንቱ ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ እየደረሱ ይገኛሉ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያን ለረጅም ዓመታት የቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ሲፈታተኗት ቆይተዋል።

እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ መገባቱ ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም የምክክር መድረኩ ለቆዩት ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በጉባኤው ተመካካሪና የጉምዝ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ግራኝ ጉደታ፤ ምክክሩ ለቀጣይ ዘላቂ ሰላምና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ምክክሩ አካታችና የጋራ መግባባትን የሚያጎለብቱ፣ እንዲሁም ለሀገር ግንባታ ጠንካራ መሠረት የሚጥሉ ሀሳቦች እየተንጸባረቁበት መሆኑን አብራርተዋል።


 

የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት (ኢዴህ) ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሔ በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ በውይይት የሚያምን ትውልድና ማኅበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

በመድረኩም ለሀገር ዘላቂ ሰላምና የጋራ መግባባት ወሳኝ የሆኑ ውጤታማ ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ጨምረው ጠቁመዋል።


 

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ ተወካይ አቶ ስማቸው እንግሶ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ይህን ያህል በርካታ ሕዝብ በአንድ ላይ ሲመካከር የመጀመሪያው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊነቷን አጠናክራ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዎንታዊ ሚና እንድትጫወት የሚያስችላት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሀሳቦችን በነጻነት ወደ መድረክ ማምጣትና በግልጽነት መነጋገር ለዘላቂ ሰላምና ሀገር ግንባታ ትልቅ መሠረት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር ናቸው።


 

ተመካካሪዎቹ በሰፊ የቡድን ውይይቶች ያነሷቸው ነጥቦች ሀገራዊ አጀንዳዎችን በስፋትና በጥልቀት ያቀፉ በመሆናቸው፣ ሂደቱ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም