የወላይታ ሕዝብ ታሪክ ተመራማሪና የሶዶ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አቶ አብራሃም ባቾሬ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የወላይታ ሕዝብ ታሪክ ተመራማሪና የሶዶ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አቶ አብራሃም ባቾሬ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 10/ 2018 (ኢዜአ)፦የወላይታ ሕዝብ ታሪክ ተመራማሪና የሶዶ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አቶ አብራሃም ባቾሬ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት ተፈጸመ፡፡
አቶ አብራሃም ባቾሬ በሕይወት ዘመናቸው በልማት፣በአስተዳደር፣በኮሙኒኬሽን፣ በባህልና ታሪክ ጥናት፣በማኅበረሰብ ዕርቅ ዘርፍ ለሀገርና ለሕዝብ ጉልህ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ እውቅና አግኝቶ በዩኔስኮ የዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ እንዲሰፍር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አየር ኃይል፣በዓለም አቀፉ የሕፃናት አቀፍ ድርጅት እና በወላይታ ልማት ማኅበር ውስጥ እንዲሁም የሶዶ ከተማ ከንቲባ በመሆን አገልግለዋል።
በተጨማሪም የወላይታ የሀገር ሽማግሌ በመሆን በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣በማስታረቅ እና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ በእድሜ ዘመናቸው የማይረሳ ታሪክ አኑረው አልፈዋል።
አቶ አብራሃም ባቾሬ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።
የወላይታ ሕዝብ ታሪክ ተመራማሪና የሶዶ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ የነበሩት አቶ አብራሃም ባቾሬ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ነሐሴ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።