ሳምንቱን በወፍ በረር!! - ኢዜአ አማርኛ
ሳምንቱን በወፍ በረር!!
ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- ሳምንቱን በወፍ በረር!!
በዚህ ዝግጅታችን በክልሎች የተከናወኑ ዓበይት ጉዳዮችን በወፍ በረር ቃኝተን እናስታውሳለን። በመሆኑም በሳምንቱ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ከተከናወኑ ዓበይት ኩነቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ምን ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?
1. የሰሊጥ ልማት በጋምቤላ
ከሳምንቱ ዓበይት ጉዳዮች መካከል በጋምቤላ ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት ከ86 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ሰብል የመልማቱ ዜና አንዱ ነው። በክልሉ የቅባት እህሎች ልማት በዋናነት በባህላዊ አርሶ አደሮችና በጥቂት ባለሀብቶች ተወስኖ ሲከናወን የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘመናዊ የግብርና ግብዓቶች እና በሜካናይዜሽን እርሻ ታግዞ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታውቋል።
እንደ ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኡጀሉ ኡሞድ ገለጻ፤ ክልሉ የቅባት ሰብሎችን ጨምሮ ለሁሉም የግብርና ልማት ሥራዎች ምቹ ስነ-ምህዳር ያለው ነው። በክልሉ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በባለሀብቶችና በአርሶ አደሮች ከ86 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ሰብል ለምቷል። ከዚህም ከ516 ሺህ ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት የሰብሉ ቁመና በተሻለ ሁኔታ ላይ ስላለ ከተጠበቀው በላይ ምርት ሊገኝ እንደሚችልም ተንብየዋል።
2. የገቢ አሰባሰብን በማጠናከር ልማትን ማፋጠን
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝብን የልማት ጥያቄ የመመለስ ተግባራት እንደሚጠናከሩ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የተገለጸውም በዚህ ሳምንት ነበር።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የተናገሩት የክልሉ ገቢዎች እና ንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች በሕገ-ወጥ የንግድ ቁጥጥር፣ ኑሮን ማረጋጋትና የታክስ ሕግ ተገዢነትን ለማረጋገጥ በሆሳዕና ከተማ ባዘጋጁት የንቅናቄ መድረክ ላይ ነው። በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በክልሉ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች የመመለስ ተግባር እንደሚጠናከር ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት ገቢን በማሳደግ የከተሞችን ገጽታ የመቀየር፣ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን የማስፋትና የማህበረሰቡን ሕይወት ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራት ስኬቶች እንደተመዘገቡና በቀጣይም ይህን ለማጠናከር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን የተሳለጠ አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት እንዳሻው (ዶ/ር)፤ ለዚህም ሕገ-ወጥነትን የመከላከል፣ የግብይት ማዕከላትን የማስፋፋት፣ ምርትን በበቂ ሁኔታ የማቅረብ፣ የዋጋ ንረትን የመቆጣጠርና የሸማች ማኅበራትን የማጠናከር ሥራዎች እንደሚከወኑም አክለዋል።
3. የአፋር ክልል በጀት
የክልሉ ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ከ33 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ያጸደቀውም በዚሁ ሳምንት ነበር። በሰመራ ከተማ ለሦስት ቀናት የተካሄደው የምክር ቤቱ 6ኛ የምርጫ ዘመን፣ 5ኛ የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔ የዳኞችንም ሹመት አጽድቋል።
የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረሳ መሐመድ በጉባዔው ተገኝተው የክልሉን የ2019 ረቂቅ በጀት ያቀረቡ ሲሆን፣ በጀቱ ከመንግሥት ድጎማ፣ ከክልሉ የውስጥ ገቢ፣ ከፌዴራል መንግሥት እና ከተለያዩ የገቢ አማራጮች የሚሸፈን መሆኑን አንስተዋል። ለበጀት ዓመቱ የተመደበው ገንዘብ የክልሉን ልማት ለማቀላጠፍና የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ይረዳል ብለዋል።
4. የኢንቨስትመንት መድረክ
ሌላው የሳምንቱ ዓበይት ጉዳይ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈጻሚ አካላት በጋምቤላ ከተማ ያካሄዱት የጋራ የምክክር መድረክ ነበር። በመድረኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢንቨስትመንት እድሎችን በማስተዋወቅና ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓቶችን በመተግበር በርካታ ባለሀብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ መቻሉም ተገልጿል።
በመድረኩም ሀገሪቱ ያሏትን የኢንቨስትመንት እድሎች ለባለሀብቶች የማስተዋወቅ እና አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎች ውጤት ማምጣታቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ በመድረኩ እንደገለጹት የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ አልሚዎችን ለመሳብ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው። በዚህም በበጀት ዓመቱ ብቻ 528 የውጭ ሀገር ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
5. የወጣቶች ተሳትፎ የላቀበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት
በየአካባቢው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸው የተገለጸው በዚሁ ሳምንት ነበር። በጅማ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳት እና ሌሎች የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን ለማከናወን በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ሕይወት በዘላቂነት ለመቀየር ያለመ ድጋፍ ተደርጓል። ከድጋፎቹ መካከል የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ፣ የምግብ ግብዓት፣ የንብ ቀፎዎች እና ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ምጣድ ይገኙበታል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ረሂማ ዩሱፍ፣ በክልሉ በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውንና በአገልግሎቱም የወጣቶች ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል። የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፤ በተያዘው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዞኑ ከ5 ሺህ 500 በላይ አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤትን ለማደስ መታቀዱንና እስካሁንም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መታደሳቸውን አንስተዋል።
6. ሚኒስቴር ተቋማቱ በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አቅመ ደካማ ለሆኑ ወገኖች ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገውም በዚህ ሳምንት ነበር። ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን እንደገለጹት፤ ድጋፉ የተደረገው በሐረር ወላጆቻቸው አቅም ለሌላቸው 600 ተማሪዎች ነው። ሚኒስትር ዴኤታው ከሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ዑመር ጋር በመሆን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ያከናወኑ ሲሆን፣ በክልሉ የአቅመ ደካማ ዜጎች መኖሪያ ቤት ግንባታንም አስጀምረዋል። ሚኒስቴሩም ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች መሰል የልማት ሥራዎችን በማከናወን ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አስታውሰዋል።
በተመሳሳይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ በተያዘው ሳምንት ነበር በዱብቲ ወረዳ አሮላፍና ገበላይቱ ቀበሌ የአቅመ ደካማ ወገኖች ቤቶች ግንባታና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ያከናወኑት። በዚህ ወቅትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ብርሐኑ ጸጋዬ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በተቀናጀ መልኩ ማከናወኑ ማህበራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስቴሩም በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአፋር ክልል 10 የአቅመ ደካማ ወገኖች መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አንስተው፣ በተጨማሪም አንድ የቅድመ መደበኛ መዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት እንደሚገነባም ነው የገለጹት።
7. የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት
ሳምንቱ በድሬዳዋ አስተዳደር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማነት ማሳደጉ የተገለጸበትም ነበር። የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ መንግሥት በተለይ የመሬት፣ የኤሌክትሪክ፣ የፋይናንስ፣ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ጥያቄዎች በአፋጣኝ እንዲመለሱ መደረጉ ኢንዱስትሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 11 ከፍተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመግባት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አንስተዋል። ኢንዱስትሪዎቹ ተኪ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ የወጪ ምርቶችን አምርተው በመላክ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ጉብኝት ከተደረገባቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል የፈሳሽና ጠጣር ሳሙና፣ የጭማቂ፣ የውሃ፣ የሮቶ፣ የካርቶንና የእርሻ መሳሪያ ማምረቻዎች እንዲሁም የቡና ማቀነባበሪያዎች ይገኙበታል።
8. ሠራዊቱ ከወገን አለኝታነቱ ባሻገር የልማት አጋርነቱን አጠናክሯል
ከሳምንቱ ዓበይት ጉዳዮች መካከል የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ዳር ድንበር የማስከበር ግዳጁን ከመወጣት ጎን ለጎን የወገን አለኝታነቱንና የልማት አጋርነቱን የሚያጠናክሩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም በዋነኝነት የተገለጸበት ነው።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ11ኛ ዕዝ አመራሮችና የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በቆቦ ከተማ እየተካሄደ ያለውን የኮሪደር ልማት ጎብኝተዋል። የ11ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አድማሱ ዓለሙ በወቅቱ እንዳሉት፤ የቆቦ ከተማ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ ዕዙ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል። በዚህም የዕዙ አመራሮችና አባላት የኮሪደር ልማቱን ለማፋጠን የወር ደመወዛቸውን 40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ድጋፉም ሠራዊቱ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ለልማት ሥራው ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር የወገን አለኝታነቱን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። የዕዙ አመራሮችና አባላት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የቆቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይለዓብ ወንድሙ፣ ድጋፉ አሁን ላይ 43 በመቶ የደረሰውን የኮሪደር ልማት ፈጥኖ በማጠናቀቅ ለህዝብ አገልግሎት ለማብቃት ያስችላል ብለዋል።
9. ኢትዮጵያን በመገንባት ረገድ የወጣቱ ሚና
ወጣቱ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁለንተናዊ ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ያሳሰቡትም በዚሁ ሳምንት ነበር።
ከንቲባው ይህን ያሳሰቡት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ27ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ በድሬዳዋ በተከበረው ዓለም አቀፉ የወጣቶች ቀን ላይ ተገኝተው ነው። በመልእክታቸውም ወጣቶች የተሻለች ሀገርን ለመገንባትና ለመረከብ እያደረጉት ያለው ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት አበረታች ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል። ወጣቶች በተለይም የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሀገር ተረካቢ የሆነውን ትውልድ ወደ ላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንደሚያሸጋግርም በመድረኩ ተገልጿል።
10. ዲጂታላይዜሽንን ለሙስና መከላከል
የመደመር መንግሥት የፈጠራቸውን መልካም እድሎች በመጠቀም ለሀገር ልማት በጋራ መትጋትና ልሹ አሰራሮችን መዋጋት እንደሚገባ የተገለጸው በተያዘው ሳምንት ነው።
የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ማጠቃለያ መድረክ "የፀረ-ሙስና ትግል ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፤ በሙስና ትግል የመጀመሪያ ምዕራፍ መከላከልን፣ ምርመራንና ክስን በአንድ ተቋም በማድረግ ይሰራ እንደነበር አስታውሰዋል። ሆኖም እንቅስቃሴው ህዝብን የትግሉ ባለቤት ያላደረገ፣ የሙስና መከላከል ስራን የረሳ እና ለትውልድ የስነ-ምግባር ግንባታ ቦታ የማይሰጥ ነበር ብለዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ፣ ከሚሊኒየም መባቻ ጀምሮ ለውጡ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የነበረው ወቅት በልማታዊ መንግሥት ስም ከፍተኛ ጣልቃገብነት የተካሄደበት እንዲሁም ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋበት እንደነበር አንስተዋል። በዚህም ምክንያት የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ ሜጋ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በሙስና እና በሌብነት ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው እንደነበር አስታውሰዋል።
በሦስተኛው ምዕራፍ፣ ከሀገራዊ ለውጡ መባቻ ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ከሙስና ትግል አኳያ መሰረታዊ ለውጥ ተደርጓል ብለዋል። በኮሚሽኑ ላይ ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከል ዋነኛው የሕግ ሪፎርም መሆኑን አንስተው፤ ሙስናን በአንድ ተቋም ብቻ መታገል ስለማይቻል ሁሉም የመንግሥት ተቋማት የትግሉ ባለቤት እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል። በተለይም የዲጂታላይዜሽንን መልካም እድሎች በመጠቀም አገልግሎቶችን ከሰው ንክኪ ነፃ እና አካታች በሆነ መንገድ ማቅረብ መቻሉና መሰረታዊ የእሳቤ ለውጥ ማምጣቱ ለፀረ-ሙስና ትግሉ ጠንካራ መሰረት እየጣለ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
11. ኢዜአ በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ባደረገላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደሰታቸውን በባህር ዳር ከተማ ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችና ወላጆች መግለጻቸው የተዘገበውም በሳምንቱ ነበር።
በወቅቱም የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ፤ ኢዜአ ከመረጃ ተደራሽነት ባሻገር በማህበራዊ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ አገልግሎት በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል። ኢዜአ የትምህርት ቤቶች ድጋፍ ላለፉት ስድስት እና ሰባት ዓመታት በተከታታይ ሲያከናውን መቆየቱን አንስተው፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና በመሰል በጎ ተግባራት ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠሉንም አክለዋል። በበባሕር ዳር ከተማ የአረንጓዴ አሻራን ከማኖር ባለፈ ኢዜአ ለ357 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስራቴ ሙጨ በበኩላቸው፤ የኢዜአ አርዓያነት ያለው ተግባር በሌሎችም ዘንድ መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልጸው፤ ለተደረገው መልካም ተግባር ሁሉ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ስም ምስጋና አቅርበዋል። ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችና ወላጆች ኢዜአ ባደረገላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው ለተደረገውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኢዜአ ከትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በባህርዳር የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት የሕንፃ ግንባታን አስጀምሯል። የሚገነባው የመማሪያ ክፍል ለታዳጊ ተማሪዎች ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ሲሉ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ የገለጹትም በዚህ ወቅት ነው።
የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምንይችል ዓለማየሁ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገር ብሔራዊ ጥቅም፣ በገጽታ ግንባታ ሥራዎች እንዲሁም የጋራና አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።ተቋሙ ከሀገራዊ ተልዕኮው ባሻገር በማኅበራዊ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይም ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ኢዜአ በባሕር ዳር ከተማ ምስራቀ ፀሐይ 1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅድመ መደበኛ ትምህርት አስተባባሪ መምህርት አያል እምቢያለ፤ በአሁኑ ወቅት በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 150 ተማሪዎች እንደሚማሩ አስታውሰዋል። አዲሱ የመማሪያ ሕንፃ ግንባታ ይህንን የተማሪዎች የክፍል ጥምርታ በማስተካከል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ከዚሁ መርሃ ግብር በተጓዳኝም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተከናወነ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን ምክንያት በማድረግም ከወጣቶች ጋር የፓናል ውይይት ተካሂዷል።