የ"ጽምዶ ጥምረት" የተለያየ እኩይ ፍላጎት ያላቸው የፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች ስብስብ ነው- የኤርትራ ሰማያዊ አብዮት ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዳዊት ተፈሪ - ኢዜአ አማርኛ
የ"ጽምዶ ጥምረት" የተለያየ እኩይ ፍላጎት ያላቸው የፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች ስብስብ ነው- የኤርትራ ሰማያዊ አብዮት ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዳዊት ተፈሪ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፦ “ጽምዶ” የተሰኘው የፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች ህብረት ባልተጣጣሙ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች የተመሠረተና በፌደራል መንግሥት ላይ ባላቸው ተቃውሞ ብቻ የተጣመረ ስብስብ መሆኑን የኤርትራ ሰማያዊ አብዮት ግንባር (EBRF) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዳዊት ተፈሪ ገለጹ።
የማዕከላዊ ኮሚቴው አባል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት የበይነ መረብ ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት፤ ህብረቱ በውስጡ በርካታ የፖለቲካ ልዩነቶችና ተቃርኖዎች ያሉበት በመሆኑ፣ እንደ አንድ ዘላቂና ጠንካራ ፖለቲካዊ ጥምረት ሊወሰድ አይገባም።
በዚህ ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና አካላትን ከመሠረቱ የሚያገናኛቸው የጋራ ራዕይ የለም፤ ብቸኛ ዓላማቸው በኢትዮጵያ የሚገኘውን ማዕከላዊ መንግሥት መጣል ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የጥምረቱ የቅርብ ጊዜ ዋና ስልት በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ሁለገብ ጫናዎችን አጠናክሮ መቀጠልና የተለያዩ ተቃዋሚ ኃይሎችን በማስተባበር የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት መሆኑን አመልክተዋል።
ዋና ግባቸው መንግሥቱን በቋሚነት ማወክና የማዳከም ሥራ መስራት ሲሆን፣ መንግስትን በመጉዳት በዚህ ጥምረት የሥልጣን ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኮሚቴው አባል አክለውም፥ የጽምዶ ስልት በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አባላቱን ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ወደ ሰፊ ግጭት ሊያስገባ የሚችል ወታደራዊ ምላሽ የማግኘት ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።
ቡድኑ መንግሥትን ወደ ግጭት ማስገባት ካልቻለ፣ከፍተኛ የውስጥ ቅሬታና እርስ በርስ የሚጋጩ ተቃርኖዎች ሊገጥሙት እንደሚችሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፣ የጥምረቱ አባላት የጋራ ለሆነ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ዓላማ ሳይሆን እናሳካዋለን ብለው ለሚያስቡት ጊዜያዊ ግቦች ብቻ የተሳሰሩ ናቸው።
አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ወይም ቁርጠኛ አይደሉም ያሉት አቶ ዳዊት፣ የአሁኑ ትብብራቸው በዋናነት በአጭር ጊዜ ፍላጎቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት ካለፉት ግጭቶች ትምህርት መውሰድ እንዳለበትና ተቃዋሚ ቡድኖች የግጭቱን ሁኔታና አካሄድ እንዲወስኑ ዕድል መስጠት እንደሌለበት አሳስበዋል።