ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተጨማሪ ሃብት ለማፍራት አስችሎናል-ተጠቃሚዎች

ጎንደር፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ) ፡-የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ኑሯቸውን ለመለወጥና ተጨማሪ ሀብት ለማፍራት እንዳስቻላቸው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተጠቃሚዎች ገለጹ።

የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የሥነ-ምግብ ደረጃን ለማሻሻልና አጠቃላይ የግብርና ምርታማነትን በጥራትና በብዛት ለማሳደግ ያለመ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው። 

መርሃ-ግብሩ በተለይም በወተት፣ በማር፣ በዶሮ እርባታ፣ በሥጋ እንዲሁም በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ የቤተሰብ ገቢን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በወገራ ወረዳ አምባ ጊዮርጊስ ከተማ በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩት አቶ አበራ ምስጋናው ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በመታቀፍ በ1 ሺህ ጫጩቶች የጀመሩትን ሥራ በርትተው በመስራት የተሻለ ገቢ ማግኘት ጀምረዋል።


 

ሥራቸውን በማስፋፋትም አሁን ላይ በአንድ ጊዜ እስከ 3 ሺህ የሚደርሱ ዶሮዎችን አሳድገው ለመሸጥ የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የከተማዋ የ02 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ማርየ ራራ በበኩላቸው፤ ከመንግሥት ሥራቸው ጎን ለጎን ባላቸው ትርፍ ጊዜ በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር መሳተፋቸው የቤተሰባቸውን ሕይወት ከመለወጡ ባለፈ ተጨማሪ ሀብት ለመፍጠር እንደቻሉ ተናግረዋል።


 

አስተያየት ሰጪዎቹ በተሰማሩበት የዶሮ እርባታ ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ ከአካባቢው አስተዳደር የተደረገላቸው የቦታና የብድር ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ምስጋናው ታከለ በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ብቻ ለ20 ሺህ 588 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።


 

ዘርፉ ሥርዓተ-ምግብን ከማሻሻል ባለፈ ዜጎች የኑሮ ሁኔታቸውን እንዲለውጡና ሀብት እንዲፈጥሩ ማስቻሉንም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም