ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ከብክነት ማዳን ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ከብክነት ማዳን ተችሏል
አዳማ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ከብክነት ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች አስታወቁ።
የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያዘጋጀው 17ኛው ሀገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ትስስር ጉባኤ ትናንት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነር ጀማል ረዲ በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ከብክነት ለማዳን ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል።
ከዚህ ውስጥም ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ሙስና መከላከል የሥራ ዘርፍ ከሕዝብ የቀረቡለትን 290 ጥቆማዎች ተቀብሎ በመመርመር፣ 80 በመቶ የሚሆኑት የሙስና ይዘት እንዳላቸው ማረጋገጡን ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎ በተወሰደው እርምጃ በአስቸኳይና በመደበኛ ሙስና መከላከል ተግባራት በአጠቃላይ ከ706 ሚሊዮን ብር በላይ ከምዝበራ ማዳን ተችሏል ነው ያሉት።
ከገንዘብ በተጨማሪም 8 ሺህ 103 ካሬ ሜትር መሬት በማዳን ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።
ብልሹ አሰራሮችንና ሙስናን የመከላከል እርምጃዎችን ለማጠናከር የጥቆማ ሥርዓቱ ዘመናዊና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የጥሪ ማዕከል የማደራጀት እና ጥቆማዎች በዘመናዊ ዳታቤዝ እንዲያዙ የማድረግ ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ በትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታና በሙስና መከላከል በኩል ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም የፀረ-ሙስና ትግሉን ከማጎልበት አንጻር የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የኅብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን አስታውቀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽነር አቶ ፌኑስ አብዱልጀባር በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ ተቋማት ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የሚያስችል ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።
በተለይም በአስቸኳይ ሙስና መከላከል በተደረገው ጥረት በድሬዳዋ አስተዳደር ድሬ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፤ የፔዳጎጂካል ቴክኖሎጂ፣ ኮምፒዩተር እና ተያያዥ አክሰሰሪዎች ግዥ ጨረታ ግልጽነት የጎደለው ሆኖ መገኘቱን ለአብነት አንስተዋል።
የግዥ ጨረታው ህጋዊ አሰራርን ያልተከተለና ውስንነት ያለበት በመሆኑም ሂደቱ ተቋርጦ፣ ተስተካክሎና ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ እንዲቀጥል መደረጉን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ የሙስና ትግሉን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ በተለያዩ አማራጮች ግንዛቤ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አመልክተው፤ ህብረተሰቡ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ብለዋል።