በአፋር ክልል የገቢ አማራጮችን የማስፋትና በቁርጠኝነት ገቢን የመሰብሰብ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የገቢ አማራጮችን የማስፋትና በቁርጠኝነት ገቢን የመሰብሰብ ተግባራት ይጠናከራሉ
ሰመራ፣ነሀሴ 10/2018 (ኢዜአ):- በአፋር ክልል በተያዘው በጀት ዓመት የገቢ አማራጮችን የማስፋትና በቁርጠኝነት ገቢን የመሰብሰብ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
የተጠናቀቀው በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙበት የውይይት መድረክ በሰመራ ተካሄዷል።
በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እንደተናገሩት፣ የክልሉን ልማት ለማቀላጠፍና የህብረተሰብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ከፍተኛ ሚና አለው።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፣ በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ የገቢ አማራጮችን የማስፋትና በቁርጠኝነት ገቢን የመሰብሰብ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ከዓመት ወደ ዓመት ገቢን የመሰብሰብ አቅም እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፣ ከለውጡ በፊት የነበረውን 790 ሚሊዮን ብር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
የመሰብሰብ አቅምን በማሳደግ በጀትን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው፣ በተለይም አመራሩ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
መተባበርንና መትጋትን ማዕከል በማድረግ የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
በያዝነው ዓመት ደግሞ የገቢ ግብርን ከፍ በማድረግ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህ ስራ ስኬታማነት በየደረጃው ያለው አመራር የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ለሕዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠቱ ተግባርን ማጠናከር ከሁላችንም ይጠበቃል ያሉት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አወል አብዱ ናቸው።
የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ ኑር ሳሊም በበኩላቸው፣ የከተማዋን የገቢ አቅም የመለየት ስራዎች መከናወናቸውንና ለፈጻሚ ባለሙያዎች ትጥቅ የሚሆናቸው ስልጠናና የልምድ ልውውጥ መካሄዱንም በመድረኩ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች የእውቅና እና የሽልማት ስነ-ስርዓት አከናውነዋል።