ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት ዕድገትን የሚያፋጥን አስደማሚ ውጤት እያመጣ ነው - ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ምሁራን

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 10/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት ዕድገትን የሚያፋጥን አስደማሚ ውጤት እያመጣ መሆኑን የአሜሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ምሁራን ገለጹ።

አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሚጉኤል እና ካሜሩናዊው የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ሊነስ ኒውል ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች አስደናቂ ዕድገትና ለውጥ አስመዝግባለች።

በአሜሪካ የካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሚጉኤል፣ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ በአዲስ አበባ የተመለከቱት ለውጥ እጅግ የሚያስደምም መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ አስደናቂ የከተሜነት ዕድገትና የልማት ለውጥ ከዚህ ቀደም ያውቋቸው የነበሩ አካባቢዎችን ገጽታ በእጅጉ በመቀየሩ እንደገና ለመለየት እንኳን እንደተቸገሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለከተማ መሠረተ ልማት የሰጠው ልዩ ትኩረት የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል።

በከተማ ልማት፣ በኢኮኖሚ ማሻሻያና በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የተመዘገቡ ውጤቶች የኢትዮጵያን የልማት ቁርጠኝነት የሚያሳዩ አስደናቂ ስኬቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፎች የወሰደቻቸው የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎችም ዕድገትን በማፋጠን አዎንታዊ ውጤት እያመጡ እንደሚገኙ አንስተዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ረገድም ኢትዮጵያ አዳዲስ የማኅበራዊ ፕሮግራሞችንና የፋይናንስ አሠራሮችን በመዘርጋት የመቋቋም አቅሟን ለማሳደግ የወሰደቻቸው እርምጃዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አፍሪካ ለድርቅና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆነችበት በዚህ ወቅት የመንግሥት ቁርጠኝነትና በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውንም አብራርተዋል።


 

በአሜሪካ ፔንሲልቬኒያ ጌቲስበርግ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ምሁር የሆኑት ካሜሩናዊው ፕሮፌሰር ሊነስ ኒውል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች አስደናቂ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የወሰደቻቸው አስደናቂ የልማት መርሃ ግብሮችም የሀገሪቱን ዕድገት ከማፋጠን ባሻገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ አቅሞችን ለመገንባት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት እያስመዘገበች ያለችው እመርታም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር የሚተርፉ ወሳኝ ተሞክሮ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግሥት በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋም ውጤታማነቱን በማሳደግ፣ አህጉራዊ የምሪት ሚናዋን አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም