አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 10/2018(ኢዜአ)፦አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአራብሳ አካባቢ የተገነባውን የንጹህ መጠጥ ውሃ መሠረተ ልማትና የኮዬ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ፕሮጀክቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በጉልህ እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የመጠጥ ውሃ እጥረትን ለመፍታት የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣የመዲናዋ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በቀን ከ910 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።
በቀጣይም ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የኮዬ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የሕብረተሰቡን ጤናና የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ጣቢያው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም መሆኑን በማንሳት፣ መሰል የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎችን በስፋት ለመገንባት መታቀዱን አስረድተዋል።
መሠረተ ልማት መገንባት ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ የተገነቡትን መሠረተ ልማቶች መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም የጋራ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ለማድረግ የተጀመሩት የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በማንሳት፣ ለፕሮጀክቶቹ እውን መሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።