ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዮብ ፍሳሽ የሚያጣራውን የኮዬ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክት አስመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዮብ ፍሳሽ የሚያጣራውን የኮዬ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክት አስመረቁ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 10/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቀን 60 ሺህ ሜትር ኪዮብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚያመርት እና በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዮብ ፍሳሽ የሚያጣራ የኮዬ ፍሳሽ ዘመናዊ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን አስመርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።
ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ በቱሉ ጉዶ፣ ለገዳዲ ክፍል 2፣ በረከት የጋራ መኖሪያ አካባቢ፣ ቦሌ አራብሳና ሌሎችም በርካታ ጉድጓዶችን በማልማት በከተማዋ ከአምስት ዓመት በፊት የነበረው 525 ሺህ ሜትር ኪዩብ በቀን የማምረት አቅም ዛሬ ላይ 910 ሺህ ሜትር ኪዩብ መድረሱን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የነዋሪዎቻችንን ጤናና ንጽህና የሚጠብቁ፣ የወንዞቻችንን ብክለት የሚቀንሱ፣ የአካባቢ ጥበቃችንን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።
አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ውብ፣ ጽዱ፣ ጤናማ፣ አረንጓዴ፣ ዘመናዊና ለትውልድ የምትመች ከተማ ለማድረግ የጀመረው ግብ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የብድር አገልግሎት ለሰጠው የዓለም ባንክ፣ እንዲሁም የውሃው መገኛ አካባቢዎችን በትብብር ለማልማት ላገዘው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል፣ ከሁሉ በላይ ዘላቂ ኑሯቸውን ሲመሩበት የነበረውን መሬት ለዚህ ታላቅ ልማት የለቀቁ አርሶ አደሮች እና ለፕሮጀክቱ ስኬት ሌት ተቀን ያለእረፍት የተጉ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አመራሮች እና ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።