ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ በሠለጠነ መንገድ መፍትሔ የመፈለግ አዲስ ባህል እንዲፈጠር አድርጓል-ትዴፓ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 10 /2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በሠለጠነ መንገድ መፍትሔ የመፈለግ አዲስ የፖለቲካ ባህል እና የመደጋገፍ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አስታወቀ።

ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ ሂደቱ ያለፉ የታሪክ ጠባሳዎችን በማከም ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መንገድ የሚከፍት መሆኑን አመልክቷል።

የትግራይ ሕዝብ ድምፅ እና እውነተኛ ፍላጎት በሀገራዊ መድረኩ ላይ እንዲደመጥ ከአጀንዳ ማሰባሰብ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር በቅርበት ሲሠራ መቆየቱን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ ከ300 በላይ የትግራይ ሕዝብ ተወካዮች በሂደቱ በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን አስታውቋል።

ፓርቲው አክሎም፥ ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን አሁንም ድረስ በሚያካሂደው የጦርነት ዜማ ምክንያት በወጣቶች ሕይወት እና የነገ ተስፋ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ ራሱን ከጦርነት እና ከጥፋት አውድ ነፃ የሚያወጣበትን አቅጣጫ መከተል እንዳለበት አሳስቧል።

ራሳቸውን ከግጭት ስጋት ለማዳን ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎች በመምጣት በከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንግልት ውስጥ ለሚገኙ የትግራይ ወጣቶች የመንግሥት አካላት፣ባለሀብቶች እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ትዴፓ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም