ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ የልማት ውጤቶች ሀገሪቱን ውብና ተወዳዳሪ የቱሪዝም ማዕከል እያደረጓት ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ10/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ የልማት ውጤቶች ሀገሪቱን ውብ ገጽታ በማላበስ ተወዳዳሪ የቱሪዝም ማዕከል እያደረጓት መሆኑን ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ገለጹ።

መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ብዝኃ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ካስቀመጣቸው አምስት የልማት አዕማድ መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ነው።

የመደመር ዕሳቤ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶችን ይዘታቸውን ጠብቀው ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ የሚያስችል አዲስ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት አቅጣጫ ቀይሷል።

አዲስ አበባን ጨምሮ ከ65 በላይ የኢትዮጵያ ከተሞች የተከናወኑ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ሀገሪቱን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ አድርገዋታል።

በተለይም የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫና የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ፣ ከንግድና ከአስተዳደር ማዕከልነት ባሻገር የሚመጥናትን የመዝናኛና የቱሪዝም መዳረሻነት ተላብሳለች።

ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ በሁሉም የከተማዋ ሥፍራዎች የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለከተማዋ አዲስ ገጽታን በመፍጠር ምቹ የጎብኚዎች መዳረሻ እንድትሆን አስችለዋታል።


 

ቤልጂየማዊው ዴሪክ ዴሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ አስደናቂ ውበት፣ ጽዳትና የሕዝቡ ሞቅ ያለ እንግዳ ተቀባይነት ጎብኚዎች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙና በሌላ ጊዜ ተመልሰው ለመምጣት እንዲያስቡ ያደርጋል።

በአዲስ አበባ ቆይታቸው እንጦጦ ፓርክንና ብሔራዊ ሙዚየምን መጎብኘታቸውን ገልጸው፣ የሆቴል አገልግሎቶች የኢትዮጵያውያንን እንግዳ ተቀባይነት በጉልህ እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።

ጣሊያናዊው አሌክሳንድሮ ቦዞ ከ20 ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን ከተማዋ ፈጣንና ማራኪ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኗን ገልጸዋል።

የወንዞች ዳርቻዎች መጥፎ ገጽታ የተላበሱ እንደነበር በመግለጽ፣ አሁን ማራኪና ንጹሕ ከመሆናቸውም በላይ ደህንነት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከቤተሰቦቼ ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው ብለዋል።


 

ጀርመናዊው ሉካስ ኩፕፈርናጌል በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበራቸው ቆይታ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች በቱሪዝም ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች አስገራሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በማስፋፋትና የመዳረሻዎችን የአገልግሎት ደረጃ በማሻሻል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የቱሪስት ማዕከል የሚያደርጋትን አቅም አሳይታለች ብለዋል።

ሌላኛው ጀርመናዊ ሄርማን ግሬሆ የአዲስ አበባ ፈጣን የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት ከተማዋን ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ምቹና ማራኪ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።


 

በብሔራዊ ሙዚየም የተመለከትኩት የሰው ልጅ ቅሪተ አካል ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የሥልጣኔ ታሪክ ባለቤት መሆኗን ከማሳየት ባለፈ ልዩ ትዝታ ፈጥሮብኛል ብለዋል።

አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት የኢትዮጵያን የበለጸገ የባህልና የተፈጥሮ ሀብት በተሻለ መንገድ ለዓለም ለማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች የመጎብኘት ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮና የባህል ሀብቷን በዘመናዊ መንገድ በማልማት፣ ቱሪዝምን ለገጽታ ግንባታ ከማዋል ባሻገር ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ምንጭ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት እየገነባች ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም