ቀጥታ፡

የአቮካዶ ልማትን በማዘመን ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል- ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር

ሐረር፣ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- የአቮካዶ ልማትን በማዘመን ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድ ሮዛ ኡመር ገለጹ።

ሀገር አቀፍ የአቮካዶ ልማት ኢኒሼቲቭ  ከሚተገበርባቸው 10 ክልሎች መካከል አንዱ የሐረሪ ክልል ሲሆን በዛሬው እለትም  በገጠርና በከተማ ክላስተሮች የአቮካዶ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተከናውኗል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የክልሉ መንግሥት በርካታ ኢኒሼቲቮችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ  ነው።

በአሁኑ ወቅትም አቮካዶን ጨምሮ ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራዎችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የአቮካዶ ልማት ኢኒሼቲቭ   ዋና ዓላማ ምርቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር  ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብን ጨምሮ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የሥራ ዕድል መፍጠር ነው ብለዋል።


 

በተለይ የክልሉ የአየር ፀባይ ለአቮካዶ ልማት ምቹ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በክልሉ የግብርና ልማት ቢሮ የብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ መሐመድ ሬድዋን ናቸው።

በችግኝ ጣቢያዎች 106 ሺህ የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን የማዘጋጀት ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ ችግኞቹን በገጠርና በከተማ በ100 ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል።


 

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉት መካከል ወጣት ማሩፋ ሙሳ እና አርሶ አደር አብዲ በያን ፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ያስገኝውን ውጤት መነሻ በማድረግ አቮካዶን ይበልጥ ለማልማት መነሳሳታቸውን ነው የተናገሩት።

አቮካዶ ልማት ሥራ ተጠቃሚነትን ከማጎልበቱ ባሻገር የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኙም ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም