ቀጥታ፡

ቀጣይነት ያለው ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል-ሚኒስትር ዴኤታ  ሙና አህመድ

ጅማ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- ቀጣይነት ያለው ሁለንተናዊ  ዕድገት ለማስመዝገብ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ  ሙና አህመድ ገለጹ።

ዓለም አቀፉ የወጣቶች ቀን "ብዝሃ የወጣቶች እውቀት፤ ለጋራ ትልም!" በሚል መሪ ሐሳብ በብሔራዊ ደረጃ በጅማ ከተማ እየተከበረ ነው።


 

ሚኒስትር ዴኤታዋ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፤ ወጣቶች የሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ሞተር ናቸው።

አክለውም በሀገራችን ቀጣይነት ያለው ሁለንተናዊ  ዕድገትን ለማስመዝገብ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

''ሀገር ጠንካራ እና ዘላቂ ሰላም የሚኖራት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ስትችል ነው።'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣  የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል የ5 ዓመት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰፋ እና ባህል እየሆነ መምጣቱን ገልፀው፣ ወጣቶች ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ለህዝባቸው እየሰጡ በመሆኑ ሀገራዊ አንድነትና የመረዳዳት እሴቱ እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል። 

በቀጣይም በሀብት እና በስራ ዕድል ፈጠራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራም ሚኒስትር ዴኤታዋ አረጋግጠዋል።


 

የኦሮሚያ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ቢያ በበኩላቸው፣ በዓሉን የምናከብረው ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ባሉበት ወቅት መሆኑን ገልፀዋል።

ወጣቶች በአካባቢያቸው ያለውን ሀብት በመጠቀም፣ የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ወደ ስራ በመቀየር ራሳቸውን መለወጥ እና ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

ወጣቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በፈጠራ ስራዎች ላይ በመሰማራት በጋራ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ለሀገራቸው ዕድገት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።


 

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር፤ የወጣቶች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በጅማ ከተማ መከበሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ለሀገር ሰላም እና አንድነት እንዲሁም ለወጣቶች ተጠቃሚነት በዞኑ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ዕለቱ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጀምሮ በፓናል ውይይት እና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች እየታሰበ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም