በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ172 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥና ማሾ ሰብል ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ172 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥና ማሾ ሰብል ለምቷል
ገንዳ ውኃ፣ ነሐሴ10/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር እርሻ ከ172 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሰሊጥና ማሾ ሰብሎችን ማልማት መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የመምሪያው ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ጌጡ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዞኑ ለወጪ ንግድና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛል።
በዚህም እስካሁን በተደረገው ጥረት በአጠቃላይ በሰሊጥና በማሾ ሰብል ከለማው ከ172 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በሰሊጥ፣ ቀሪው ደግሞ በማሾ ሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ልማትም ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
ምርታማነቱን ለማሳደግም ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና የመካናይዜሽን አስተራረስ ዘዴዎችን በመጠቀም መዝራት መቻሉን ጠቁመዋል።
በሰብል ልማቱ ከ59 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና 500 የሚደርሱ ባለሀብቶች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸው፣ የአረምና የተባይ መከላከል ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብም በቅድመና ድህረ-ምርት አያያዝ ላይ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ አብራርተዋል።
በዞኑ የመተማ ወረዳ አርሶ አደር አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው፣ ዝናብ ዘግይቶ ቢጥልም የተገኘውን እርጥበት በመጠቀም አራት ሄክታር መሬታቸውን በሰሊጥ መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
በኩታ ገጠም አስተራረስና በዘመናዊ መካናይዜሽን ተጠቅመው ካለሙት ሰብልም ከ30 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
ሌላው የመተማ ወረዳ አርሶ አደር ደሳለኝ ገብሬ፣ በዘንድሮው የመኸር እርሻ የግብዓት አቅርቦት በወቅቱ መድረሱ ማሾና ሰሊጥን በስፋት ለማልማት መቻላቸውን ገልጸዋል።
አሁንም ዋና ትኩረታቸው ሰብሉን ከተባይ መጠበቅና ምርቱን ከብክነት በጸዳ መልኩ ሰብስቦ ለገበያ ማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፈው የምርት ዘመን ከ163 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ሰብል ለምቶ ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።