በሰሜን ሸዋ ዞን 543 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመኸር እርሻ ለማልማት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን 543 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመኸር እርሻ ለማልማት ተችሏል
ደብረ ብርሃን፤ ነሃሴ 10/2018(ኢዜአ)፡- በሰሜን ሸዋ ዞን በመኸር እርሻ 543 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት የእንክብካቤ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ተውልኝ ሽባባው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በክረምቱ ወቅት በአጠቃላይ 563 ሺህ 043 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
እስካሁን በተደረገ ጥረትም 542 ሺህ 960 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል።
ከ332 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የተካሄደው የዘር ስራ ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር ከ96 በመቶ በላይ መሳካቱን ተናግረዋል።
በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥም 288 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በጤፍ፣ ስንዴ፣ ባቄላና ማሾ ሰብሎች በኩታ ገጠም የአሰራር ዘዴ የለማ መሆኑን ባለሙያው አረጋግጠዋል።
ዝናብ ዘግይቶ ቢጥልም፣ በግብርና ባለሙያዎች የተጠናከረ ድጋፍ አርሶ አደሩ ሌት ተቀን እንዲረባረብ በማድረግ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግም 720 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 109 ሺህ 222 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን አቶ ተውልኝ አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅትም የለማውን ሰብል በማረም፣ተባይን በመከላከልና በመንከባከብ ተግባር ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዞኑ የሞረትና ጅሩ ወረዳ የገርባ ቀበሌ አርሶ አደር መዝገቡ ወልዴ በበኩላቸው፣ ሰባት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬታቸውን በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በመጠቀም በስንዴና አተር ሰብል መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ቴክኖሎጅዎችን ከመጠቀም ባሻገር፣ የአረምና የተባይ መከላከል ስራ እያካሄዱ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዞኑ የመርሐቤቴ ወረዳ ሰባጌ ሀሮ ገንዳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ቄስ አውግቸው ማሞ በበኩላቸው፣ መሬታቸውን በኩታ ገጠም አሰራር ተጠቅመው በጤፍ፣ ማሽላና ባቄላ ሰብል መሸፈናቸውን አስታውቀዋል።
ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በዞኑ ከ2018/19 የመኸር ምርት ዘመን 20 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።