አርሰናል ከማንችስተር ሲቲ የኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫን ለማንሳት የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ከማንችስተር ሲቲ የኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫን ለማንሳት የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10 /2018 (ኢዜአ):- የ2026 የኮሙኒቲ ሺልድ የዋንጫ ጨዋታ በአርሰናል እና ማንችስተር ሲቲ መካከል ዛሬ ይካሄዳል።
ጨዋታው ከቀኑ 11 ሰዓት በዌልስ መዲና ካርዲፍ በሚገኘው ታሪካዊው ፕሪንሲፓሊቲ ስታዲየም ይካሄዳል።
ይህ ተጠባቂ የውድድር ዘመን መክፈቻ ጨዋታ የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነውን አርሰናልን እና የ2026 የኤፍኤ ካፕ አሸናፊውን ማንቸስተር ሲቲን ያገናኛል።
አርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ክብር በመቀዳጀት፣ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በኤፍኤ ካፕ ፍፃሜ ቼልሲን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለዛሬ ጨዋታ ቀርበዋል።
በኮሙኒቲ ሺልድ ታሪክ አርሰናል በማንቸስተር ሲቲ ላይ ፍጹም የበላይነት እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በዚሁ መድረክ ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን በሶስቱም ጨዋታዎች አርሰናል አሸንፏል።
ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2023 ባደረጉት የኮሙኒቲ ሺልድ ጨዋታ አርሰናል በመለያ ምት ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ጨዋታው ከዚህ ቀደም በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲየም ይደረግ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ዌልስ መዲና ካርዲፍ በሚገኘው ታሪካዊው ፕሪንሲፓሊቲ ስታዲየም እንዲዘዋወር ተደርጓል።
ይህም የሆነበት ምክንያት በዌምብሌይ ስታዲየም ቀድሞ የተያዘ የሙዚቃ ኮንሰርት በመኖሩ እንደሆነ ታውቋል።
ይህም ውድድሩ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዌልስ መዲና እንዲመለስ አድርጎታል።
የ34 ዓመቱ ሳም ባሮት ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
የኮሙኒቲ ሺልድ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1908 "የኤፍኤ ቻሪቲ ሺልድ" በሚል ስያሜ የነበረ ሲሆን በኋላም እ.ኤ.አ በ2002 አሁን ወደሚጠራበት "ኤፍኤ ኮምዩኒቲ ሺልድ" ስያሜ ተቀይሯል።
ውድድሩ የሊጉን ሻምፒዮን እና የኤፍኤ ካፕ አሸናፊውን በማገናኘት አዲሱ የውድድር ዘመን በይፋ መጀመሩ የሚበሰርበት ነው።
ከጨዋታው ትኬት ሽያጭ እና ማስታወቂያ የሚሰበሰበው ገቢ በሙሉ በእንግሊዝ ዙሪያ ለሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና የማህበረሰብ እግር ኳስ ልማት ስራዎች ይውላል።
ማንቸስተር ዩናይትድ 21 ጊዜ በማሸነፍ የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ነው።
አርሰናል 17 ዋንጫዎችን በማንሳት ይከተላል። ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ሰባት ጊዜ አሸንፏል።