በአፋር ክልል ገቢን በተቀናጀ መንገድ የመሰብሰብ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል ገቢን በተቀናጀ መንገድ የመሰብሰብ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
ሰመራ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል ገቢን በተቀናጀ መንገድ የመሰብሰብ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡመር ኑር ተናገሩ።
በክልሉ ያለፈው በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡመር ኑር እንዳሉት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የክልሉን ገቢ በቅንጅት የመሰብሰቡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የበጀት ዓመቱን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት በሚከናወኑ ቅንጅታዊ ሥራዎች በየደረጃ የሚገኘው አመራር ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።
ለመሰብሰብ የተያዘውን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት የግብር ስወራን በቅንጅት ከመቆጣጠር ባለፈ ህብረተሰቡ ግብሩን በተለያዩ አማራጮች እንዲከፍል ግንዛቤውን የማሳደግ ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የገቢ ዕቅዱን ለማሳካት ባለፈው ዓመት በቅንጅት በተከናወኑ ሥራዎች የተገኘውን ወጤት በመቀመር ይሰራል ሲሉም አክለዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አወል አብዱ በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ከዓመት ወደ ዓመት ገቢን የመሰብሰብ አቅም እያደገ መምጣቱን ገልፀው የዘንድሮውን ዓመት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሰብስቦ ለማጠናቀቅ በትጋት ይሰራል ብለዋል።
አመራሩ ለገቢ ዕቅዱ መሳካት በተናበበ መልኩ ከመስራት ባለፈ ለሚያጋጥሙ ችግሮች በጋራ መፍትሄ እየሰጠ መሄድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በተለይም ከዚህ ቀደም የሚስተዋሉ ደረሰኝ አለመቁረጥና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ለንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ እየሰተጠ መሆኑንም አመልክተዋል።
ክልሉ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ የሚታወስ ነው።