አጀንዳዎችን የማደራጀቱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
አጀንዳዎችን የማደራጀቱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦችን የመለየትና የማጣጣም ሥራ ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ።
ስምንቱ ባለ 500 አባላት ቡድኖች ያዘጋጇቸውንና የተስማሙባቸውን ምክረ-ሀሳቦች እንዲያናብብ፣ እንዲያጣጥም እና እንዲያደራጅ ለተቋቋመው እና 120 አባላት ላሉት ቡድን ትላንት ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
ዛሬም 120 አባላት ካሉት ቡድን የተመረጡ 34 አባላት በስምንት ንዑስ ቡድኖች ተከፋፍለው የእያንዳንዱን የአጀንዳ ሃሳቦችን በጥልቀት ሲመረምሩ መዋላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
አባላቱ በተለያዩ አጀንዳዎች ስር በተደጋጋሚ የተነሱ ሃሳቦች እንዳይኖሩ የመለየት፣ ያለ ምድባቸው የተነሱ ሃሳቦችን ወደሚመለከታቸው የአጀንዳ ምድብ የመመለስ እንዲሁም የማጥራትና የማጣጣም ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን አመልክቷል።
ይህ ስራ የሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ምክረ ሃሳቦችን ወጥ በሆነና ጥራት ባለው መልኩ ለማደራጀት የሚያግዝ እንደሆነ ተገልጿል።
አጀንዳዎችን የማደራጀት ሂደት እስከ ነገ እንደሚቀጥልም የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።