የኮሪያ–ኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ሕክምና የአጋርነት ፕሮግራሞች የልዩ ሕክምና አገልግሎትን ለማስፋፋትና የሰው ኃይል አቅምን ለማጠናከር ወሳኝ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪያ–ኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ሕክምና የአጋርነት ፕሮግራሞች የልዩ ሕክምና አገልግሎትን ለማስፋፋትና የሰው ኃይል አቅምን ለማጠናከር ወሳኝ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የኮሪያ–ኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ሕክምና የአጋርነት ፕሮግራሞች የልዩ ሕክምና አገልግሎትን ለማስፋፋትና የሰው ኃይል አቅምን ለማጠናከር ወሳኝ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የኮሪያ-ኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ሕክምና ሥልጠና ፕሮግራም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ቀዶ ሕክምና አቅምን በማሳደግና የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን በማብቃት ጉልህ ውጤት ማስመዝገቡም ተመላክቷል።
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ላለፉት 10 ዓመታት ለተከናወነው የልብ ቀዶ ህክምና የአቅም ግንባታ ሥልጠና የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ፣ ትብብሩ ከአጭር ጊዜ ሕክምና ድጋፍ ባለፈ ዘላቂ የባለሙያ አቅም ግንባታ ስራን ማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።
እንደነዚህ ያሉ የአጋርነት ፕሮግራሞች የልዩ ሕክምና አገልግሎትን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ፣ የባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት እንዲሁም የመሣሪያና የመሠረተ ልማት ዝግጅቶችን ይበልጥ በማጠናከር በኢትዮጵያ የልብ ሕክምናን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ጂም ኮንግ በበኩላቸው፣ ፕሮግራሙ ከተጀመረ ከአምስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች በራሳቸው የልብ ቀዶ ሕክምና ማከናወን መጀመራቸው የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የልብ ህክምና ባለሙያዎች በዓመት ከ150 በላይ የልብ ቀዶ ሕክምናዎችን እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም የ10 ዓመቱ ትብብር የዕውቀት ሽግግርና የአቅም ግንባታ ውጤት እንደሆነ ገልጸዋል።
የኮሪያ እና የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን ትብብር በማጠናከር ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የልብ ሕክምና ባለሙያዎች የሥልጠና ማዕከል እንዲሆን የሚያስችል ሥራ ለማስፋፋት ዕቅድ መኖሩ ተገልጿል።
ፕሮግራሙ በቀጣይ የበለጠ የላቀ የልብ ቀዶ ሕክምና፣ ሥልጠና፣ ምርምርና የሕክምና አገልግሎት ትብብርን ለማስፋፋት እንደሚሰራም ተጠቁሟል።