ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የዳኞችና ዐቃቤያነ-ህግን ሙያዊ ዕውቀት ለማጎልበት የበይነ-መረብ ስልጠና ሊሰጥ ነው

አዳማ፤ ነሐሴ  09/2018 (ኢዜአ)፦ የፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት የዳኞችና ዐቃቤያነ-ህግን ሙያዊ ዕውቀት ለማጎልበትና ክህሎታቸውን ለማዳበር የሚያስችል የበይነ-መረብ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጥ መሆኑን ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ የበይነ-መረብ ትምህርትና ስልጠናውን ለማስጀመር የተዘጋጁ ኮርሶችንና ሞጁሎችን በየደረጃው ለሚገኙ የፌዴራልና የክልል የፍትህ ሴክተር አመራሮች እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት የማስተዋወቅና ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዳማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዘካሪያስ ኤርኮላ(ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ኢንስቲትዩቱ ከገፅ ለገፅ ስልጠና አሰጣጥ ዘዴ በመውጣት በቴክኖሎጂ ወደ ተደገፈ የበይነ መረብ ስልጠና ለመሻገር ነው ብለዋል።

የመደመር መንግሥት የ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ ግቦችን ለማሳካት የኢንስቲትዩቱን የስልጠና አሰጣጥ ሂደትን ወደ ''ኢ-ለርኒንግ'' ለማሻገር ያለመ የበይነ መረብ ስልጠና ማስጀመሪያ ፕሮግራም መሆኑንም  ተናግረዋል።

ለዚህም ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የፍትህ ሚኒስቴር የህግ ሙያተኞችና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ስድስት የዲጂታል ኮርሶች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ዳኞችና የፍትህ አካላት በስራ ቦታ ላይ ሆነው ባላቸው ኮምፒውተር፣ ስማርት ስልኮችና ታብሌቶች ስልጠናውን መውሰድ ይችላሉ ብለዋል።

ይህም ዳኞች ባሉበት ቦታ ሆነው በህግ ላይ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ እንዲሁም አቅማቸውን እንዲገነቡ ያስችላቸዋል ብለዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ለሊሴ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጀው የበይነ-መረብ ስልጠና ዳኞችና ዐቃቤያነ-ህግ የህግ ክህሎታቸውን በማዳበር መሰረታዊ አቅማቸውን እንዲገነቡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንስቲትዩቱ የስልጠና ሂደት በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ መደረጉ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ግቦችን ለማሳካት የተጀመረውን ጉዞ የሚያፋጥን ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

የፍርድ ቤት ኬዞች ምዝገባ፣ የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት፣ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት፣ የክርክር አመራር፣ እንዲሁም የማስረጃ አሰማምና አቀራረብን ጨምሮ ስድስት ኮርሶች መዘጋጀታቸው ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ በበኩላቸው፤ የበይነ-መረብ ስልጠናው የዳኞችንና የፍትህ አካላትን ሙያዊ ብቃት ባሉበት ሆነው ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የፍርድ ቤት ዳኞች ስራ የሚበዛባቸው በመሆኑ፣ ከስራ ገበታቸው ሳይርቁ ባሉበት ቦታ ሆነው አቅምና ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ስልጠናው የፍትህ አገልግሎቱን ጥራት ለማስጠበቅ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በየደረጃው ያሉ የክልሉ ዳኞች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የሐረር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አኢሻ ሚኔ ዑመር በበኩላቸው ያለንበት ዘመን የዲጂታላይዜሽንና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ የበይነ መረብ ትምህርትና ስልጠና ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

የበይነ-መረብ ስልጠና መርሃ ግብሩ ዳኞችና የፍትህ አካላት ከወቅቱ ጋር በመራመድ ራሳቸውን በዕውቀትና በክህሎት እንዲያበቁ የሚያስችል መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም