ቀጥታ፡

በድሬዳዋ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመፍታት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመፍታት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አብዲ ሙክታር ገለጹ።

ምክር ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የምግብና እና የትምህርት መርጃ ቁሶችን ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉን ለአቅመ ደካማ ቤሰቦችና ወላጆቻቸው አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች እያስረከቡት የምክርቤቱ አፈጉባኤ አብዲ ሙክታር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና ሌሎች የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።


የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አብዲ ሙክታር በወቅቱ እንዳሉት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በተቀናጀ መንገድ እየፈቱ ናቸው።


እርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶችን በማጠናከር የአቅመ ደካሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመፍታት ሥራ በተያዘው ክረምትም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስገንዝበዋል።


በዛሬው ዕለትም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የተገዙ የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ወላጆቻቸው አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች መሰጠቱን አመልክተዋል።


በተጨማሪም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የተገዙ የምግብ ድጋፎች ለ250 ችግረኛ ቤተሰቦች መከፋፈሉን ነው የገለጹት።


ምክርቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ባለሃብቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ደም በመለገስ፣ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ እንዲሁም የአረጋውያንን ቤቶች በማደስና በመገንባት እየተሳተፉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።


በድጋፍ ሥነስርአቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው እንዳሉት በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ማህበረሰቡ፣ ሴክተር ተቋማትና ባለሃብቶች በቅንጅት እየተሳተፉ ይገኛሉ።


በአገልግሎቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የዜጎችን መሰረታዊ ችግሮች ከመፍታት ባለፈ የሀገርን የልማት እንቅስቃሴ ያግዛሉ ብለዋል። 


የዛሬው ድጋፍ እርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል መገለጫ መሆኑን አንስተው፣ ይሄ መልካም ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።


የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ14 የልማት አይነቶች በተቀናጀ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተባባሪና የአስተዳደሩ የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ ናቸው።


እነዚህን ውጤታማ ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ከፍታ ዕውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።


የትምህርት ቁሶች ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ኢክራም አብዱረህማን እና ተማሪ አለማየሁ ታደሰ እንዳሉት፤ የተደረገላቸው ድጋፍ በአዲሱ ዓመት ትምህርታቸውን ያለሀሳብ ለመከታተል ያስችላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም