የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ህዝቡ የጸረ ሙስና ትገሉ ባለቤት እየሆነ መምጣቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ህዝቡ የጸረ ሙስና ትገሉ ባለቤት እየሆነ መምጣቱን አስታወቀ
አዳማ፤ ነሐሴ 09/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ ግንዛቤ ለመፍጠር በተሰሩ ስራዎች ህዝቡ የጸረ ሙስና ትገሉ ባለቤት እየሆነ መምጣቱን የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ኮሚሽኑ ያሰናዳው በ17ኛው ሀገር አቀፍ የሥነምግባርና የፀረ- ሙስና ኮሚሽኖች ትስስር ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል።
በጉባዔው ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በፀረ ሙስና እና ስነ ምግባር ረገድ በተከናወኑት ተግባራት ዋነኛውና ትልቁ ማእቀፍ የሆነው የትውልድ ሥርዓት ግንባታ ጥሩ አቅጣጫ ይዟል።
በዚህ ረገድ በፀረ ሙስና ትግል ዙሪያ በየደረጃው ለሚገኘው ሕዝብ ግንዛቤን ለማስረፅ በተሰራው ስራ ህዝቡ የሙስና ትግሉ ባለቤት እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
ህዝቡ ሙስና በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የሰላም አለመረጋጋትን ከሚፈጥሩ ችግሮች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ተግዳሮት መሆኑን በጽኑ አቋም በማመን መንግሥት ችግሩን እንዲገታ ያላውን አቋም በተለያዩ መድረኮች ማሳወቁ ለፀረ ሙስና ትግሉ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።
አሁን ላይ መንግሥት በሙስና ላይ የያዘው አቋምና እርምጃ ችግሩን ለማስወገድ ወሳኝ መሆኑን የነሱት ኮሚሽኑ፤ በተለይም ትግሉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ጊዜው የሚጠይቀውን የአሰራር፣ የትብብርና የቅንጅት ስራን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
ኮሚሽኑ ባለፈው በጀት ዓመት የፀረ ሙስና ትግሉ በሥነ ምግባር ግንባታ፣ ሙስናን አስቀድሞ መከላከልና ሕግ ማስከበር እንዲሁም የአንድ ዕቅድ የአንድ ሪፖርት ስትራቴጂዎች በመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ አፈጻጸም ማከናወኑን አብራርተዋል።
ኮሚሽኑ በፀረ-ሙስና ትግሉ ሚና ያላቸውን አካላት በመምራት እና በማስተባበር በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየያታቸውን ጠቅሰው፤ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ዘርፉን ከመደገፍ ረገድ ያለውን ውስንነት በቀጣይ ሊያርም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልልና የከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽኖች ቀደም ሲል 16 ዙር ሀገር አቀፍ የትስስር ጉባኤዎች መካሄዳቸው ለጸረ ሙስና ትግሉ ፍሬያማ እንዲሆን ምቹ መደላድል መፍጠሩንም አንስተዋል።
በ17ኛው ጉባዔም በ2018 በጀት ዓመት ሲከናወኑ በነበሩ የሥነ ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ስራዎች በጥልቀት በመወያየት ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በጉባዔው ላይ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ ሪፖርት ያቀረቡት በኮሚሽኑ የዲጂታል ሙስና መረጃ አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን በላይነህ፤ የ2018 በጀት ዓመት የፀረ-ሙስና ትግል በዘርፍ-ተኮር፣ ችግር ፈቺ እና ተቋማዊ አሰራር ላይ በማተኮር መከናወኑን አስታውቀዋል።
በዓመቱ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከላከል ሥራዎች ለማስፈጸም የአቅም ግንባታና ሥልጠናዎች፣ የሙስና መከላከል ጥናቶች፣ የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ተግባራት፣ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ሥራዎች በፌዴራል ተቋማትና በሕዝባዊ ድርጅቶች በተጠናከረ ሁኔታ መፈጸማቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑ ከሕግ አስከባሪ ተቋማት ጋር ትስስሩን በማጠናከር ከተለያዩ ምንጮች የሙስና ወንጀል መረጃ በመሰብሰብና በመተንተን ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረቡንም አውሰተዋል።
በመድረኩ ላይ ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።