ፖሊስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በመጠቀም የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ችሏል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ፖሊስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በመጠቀም የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ችሏል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ ፖሊስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በመጠቀም የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት 2ኛ ዙር እጩ መኮንኖችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ፖሊስ የላቁ ቴክኖሎጂዎችንና ዘመናዊ አሰራሮችን ስራ ላይ በማዋል የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ችሏል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ራሱን በሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በአሰራር እያዘመነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም የዚሁ የሪፎርም አካል መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሰልጣኞች በስልጠና ወቅት ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ህዝባቸውን በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉም አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ደኔሮ በበኩላቸው በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ የሚያስችል ሰፊ ተቋማዊ ሪፎርም መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም አዳዲስ አደረጃጀትና መዋቅሮችን መተግበሩን ጠቅሰዋል፡፡
በዓመቱ የተካሄዱ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ ህዝባዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት፣ ታላላቅ ስፖርታዊ ውድድሮች እና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች በሰላም መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ይህም በህዝቡ ንቁ ተሳትፎ፣ በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እና በጸጥታ አካላት ቅንጅት የተገኘ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
ለተመራቂ ዕጩ መኮንኖች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈው፣ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት፣ ክህሎት እና ፖሊሳዊ ስብዕና በመጠቀም ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሰለሞን ፋንታሁን እንዳሉትም ተመራቂዎች በንድፈ ሀሳብና በመስክ ስልጠና፣ የከተማ ውስጥ ኦፕሬሽን፣ የካርታ ንባብ እና የጂፒኤስ አጠቃቀምን ጨምሮ በርካታ ተግባራዊ ልምዶችን መቅሰማቸውን ተናግረዋል።
ተመራቂዎቹ በስልጠና ቆይታቸው ከመደበኛው ስልጠናና ትምህርት ጎን ለጎን በራሳቸው ተነሳሽነትና አጋሮችን በማስተባበር በቆይታቸው የልማት ሥራዎች ላይ በገንዘብና በጉልበታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።