ቀጥታ፡

የባህር ዳር ስታዲየም ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጊዜያዊ ፈቃድ አገኘ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የባህር ዳር ስታዲየም ለ27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጊዜያዊ ፈቃድ ማግኘቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቅርቡ በባህር ዳር ስታዲየም ላይ ያደረገውን ፍተሻ እና ግምገማ ተከተሎ ብሄራዊ ቡድኑ በመስከረም ወር 2019 ዓ.ም በሜዳው ለሚያደርገው ጨዋታ የሚያገለግል ጊዜያዊ የካታጎሪ 3 ፈቃድ መስጠቱን ዛሬ ለፌዴሬሽኑ በላከው ደብዳቤ አመልክቷል።

ይህ ጊዜያዊ ፈቃድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚጠብቀውን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሜዳው ጨዋታን በሀገሩ እንዲያደርግ የሚያስችለው ነው።

ካፍ በስታዲየሙ የተመዘገቡ መሻሻሎችን በማድነቅ በላከው ደብዳቤ አሁንም ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጿል።

የተቆጣጣሪ ቡድኑን ግኝቶችና የሚቀሩ የማስተካከያ እርምጃዎችን የያዘ ሙሉ ቴክኒካዊ ሪፖርት በቅርቡ ለፌዴሬሽኑ እንደሚላክ ገልጾ ጨዋታው በሚደረግበት ቀን የስታዲየሙን ዝግጁነት እና የደንቦች አተገባበር ለመከታተል የስታዲየም ተቆጣጣሪ ሊመድብ እንደሚችልም አስታውቋል።

ካፍ አያይዞም ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለስታዲየሙ አስተዳደር እና ለሚመለከታቸው አካላት በሂደቱ ላደረጉት ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም