ቀጥታ፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ተልዕኮውን በብቃት ከመወጣት ባለፈ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ያጠናክራል

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ) ፦ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ተልዕኮውን በብቃት ከመወጣት ባለፈ ማህበራዊ ሃላፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ።

የአገልግሎቱ አመራርና ሰራተኞች በ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር  በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለአንድ ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አካሂደዋል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ ስራዎች ባህል እየሆኑ መጥተዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ እርስበርስ የመተባበር፣የመረዳዳትና አንዱ ለአንዱ የመድረስ ባህል እንዲዳብር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።

ከችግኝ ተከላ ጋር በተያያዘም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉት ችግኞች የምግብ ዋስትና እያረጋገጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አገልግሎቱም ባለፉት ዓመታት በበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን አንስተዋል።

በዛሬው ዕለትም በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ ፓርክ በመገኘት ለአንድ ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የአገልግሎቱ አመራርና ሰራተኞች በእንጦጦ ፓርክ  ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።

በዚህም ለነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች በየአመቱ የሚያደርገውን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና የተተከሉ ችግኞች የመከታተል ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች በበኩላቸው በተደረገላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተሰማቸው ደስታ ገልፀዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ተማሪ ደረጀ አሸብር የተሰጠው የትምህርት ቁሳቁስ በመበረታታት ተምሮ ትልቅ ደረጃ በመድረስ ሃገሩን እንደሚረዳ ገልጿል።

ሌላናው አስተያየት ሰጪ ተማሪ ዳንኤል ግርማ በበኩሉ የተደረገው ድጋፍ የተማሪዎችን ተነሳሽነት በመጨመር ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ያግዛል ብሏል።

ድጋፉ ጠንክሮ በመማር ትልቅ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግለት የገለፀው ደግሞ ሌላኛው ተማሪ ጆን አቡነ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም