ቀጥታ፡

የሰው ዘር መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ በመምጣታችን ተደስተናል - የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን

አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የሰው ዘር መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ በመምጣታቸው መደሰታቸውን የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።

የታዳጊዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ስለ ሀገራቸው ባህል፣ ታሪክና ማንነት በአግባቡ እንዲረዱ የሚያስችል መሆኑን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።

የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን፣ ታዳጊ ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸውን ያካተተ የዳያስፖራ አባላት አዲስ አበባ ገብተዋል።

አባላቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ከሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች መካከል ማቲዎስ ዘውዱ ወደ እናት ሀገሩ ሲመጣ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጾ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ኩራት እንደሚሰማው ተናግሯል።

በሌላ በኩል፣ ታዳጊው ካሌብ ተስፋዬ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ የተሰማውን ታላቅ ደስታ በመግለጽ ኢትዮጵያ ድንቅና ውብ ሀገር መሆኗን መስክሯል።

እንዲሁም ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ሲመጣ በተደረገለት ደማቅ አቀባበል እጅግ መደሰቱን የተናገረው ደግሞ ሌላው ትውልደ ኢትዮጵያዊ እዮስያስ ተፈሪ ነው።

የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች ኢትዮጵያ የሰው ዘርና የቡና መገኛ፣ የእንግዳ ተቀባይነት ተምሳሌት ሀገር መሆኗንም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ይህንን ድንቅ ሀብት እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ከታዳጊ ቤተሰቦች መካከል ሙሉወርቅ ሽፈራው
እንዳሉት የታዳጊዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ስለ ሀገራቸው ባህል፣ ታሪክና ማንነት በአግባቡ እንዲረዱ የሚያስችል ነው።

የዳያስፖራ አባላቱ አስተባባሪ፣ የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና በአሁኑ ወቅት በካናዳ የዳያስፖራ ልጆች ስፖርት አሰልጣኝ አሸናፊ ግርማ፣ የሁለተኛ ትውልድ ዳያስፖራ አባላቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የአንድ ወር ቆይታ የስፖርት ውድድር እንደሚያደርጉና የተለያዩ አካባቢዎችን እንደሚጎበኙ ገልጸዋል።

ጉብኝቱ ታዳጊዎቹ የበለጠ ስለ ሀገራቸው እንዲገነዘቡ የሚያደርግ ነውም ብሏል።

የቀድሞ ኢንተርናሽናል ዳኛና የብሔራዊ ቡድን በረኛ ትርሃስ ገብረዮሐንስ በበኩሏ የሁለተኛው ትውልድ ታዳጊ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት ቆይታ ሀገርና ባህላቸውን የበለጠ ለማወቅ የሚያስችል ነው ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም